ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲቢኢ ኑር ‘ሐጅ ለሁሉም ለበይክ’ የቁጠባ ሂሳብ አገልገሎት መስጠት ጀመረ

ሐምሌ 01/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲቢኢ ኑር ''ሐጅ ለሁሉም'' ለበይክ የቁጠባ ሂሳብ አገልገሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።

በባንኩ የሲቢኢ ኑር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኑር ሁሴን እንደገለጹት፤ የቁጠባ ሂሳቡ አገልገሎት የሸሪዓ ህግን ያሟላ ነው።

የቁጠባ ሂሳቡ ደንበኞች በህይወት ዘመናቸው አንድ ጊዜ የሐጅ ጉዞ የማድረግ ግዴታቸውን እንዲወጡ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸው፤ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በቅርቡ የሚከበረውን የአረፋ በዓል ምክንያት በማድረግ መከፈቱን ተናግረዋል።

ከዛሬ ጀምሮ በይፋ የተጀመረውን አገልግሎት የማስተዋወቅና የንቅናቄ ስራ ለአንድ ወር እንደሚካሔድም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲቢኢ ኑር አገልግሎት ከሚሰጥባቸው 1 ሺህ 650 ቅርንጫፎች መካከል 75ቱ በዛሬው እለት የለበይክ የቁጠባ ሂሳብ አገልግሎት መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እንድሪስ “በእምነቱ አስተምሕሮ መሰረት ሁሉም የእምነቱ ተከታይ የሐጅ  ስነ-ስርአትን የመፈጸም ግዴታ አለበት” ብለዋል።

ይህንን ግዴታው ለመፈጸምና ከፈጣሪው በረከትን ለማግኘት ህዝበ ሙስሊሙ የተለያዩ ጥረቶችን እንደሚያደርግም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ''ለበይክ የቁጠባ ሂሳብ'' ተግባራዊ በማድረግ አማራጭ ይዞ በመምጣቱ አመስግነዋል።

የዘንድሮው የሐጅ ጉዞ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ማካሄድ ባይቻልም ቁጠባውን በመጀመር ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። ዜጎች ሃይማኖታዊም ሆነ የእለት ተለት የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የቁጠባ ባህላቸውን ማዳበር ይገባቸዋል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም