በጅግጅጋ ከተማ የተከሰተው ቀውስ የዜጎችን ሰብአዊ መብት ጥያቄ ውስጥ የሚከት እንደሆነ ኮሚሽኑ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በጅግጅጋ ከተማ የተከሰተው ቀውስ የዜጎችን ሰብአዊ መብት ጥያቄ ውስጥ የሚከት እንደሆነ ኮሚሽኑ ገለጸ
አዲስ አበባ ሀምሌ 30/2010 በኢትዮ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ በከተማዋ የሚኖሩ ዜጎችን ሰብአዊ መብት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባና አደጋ ላይ እንዲወድቅ እያደረገ በመሆኑ በፍጥነት መቆም እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በጅግጅጋ ከተማ ከተከሰተው ብጥብጥና ሁከት ጋር በተያያዘ ያሉ የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን አስመልክቶ ዛሬ በኮሚሽኑ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የኮሚሽኑ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ እንደገለጹት፤ በከተማዋ የተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ ዜጎች ያላቸውን ሰብአዊ መብት ተግባራዊ እንዳያደርጉ እያደረገ ነው። በከተማዋ ያሉ ዜጎች ንብረት የማፍራትና ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ከዛም አልፎ በህይወት የመኖር መብታቸውን አደጋ ላይ እየጣለ መሆኑንና የመብታቸው ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል ብለዋል። ይህ ኢ-ሰብአዊነት የተሞላበት ተግባር የዜጎችን መብት የሚነካ በመሆኑ በፍጹም ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ በፍጥነት መቆም እንዳለበት ገልጸዋል። ኮሚሽኑ ነገሮች ከረገቡ በኋላ ምርምራ በማድረግ በጉዳዩ ዙሪያ ያሉ መረጃዎችን ይፋ እንደሚያደርግ ገልጸው አሁን ባለው ሁኔታ በሰው ላይም ይሁን በንብረት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለመግለጽ እንደሚያስቸግር ተናግረዋል። በአጠቃላይ ለተከሰተው ጉዳይ ተጠያቂው ማነው? የሚለውን ጉዳይ ጥልቀት ያለው ምርመራ ማድረግ የሚጠይቅና መረጃዎችን ማደራጀት እንደሚያስፈልግም ነው አቶ ደምሰው ያስረዱት። በክልሉ እየደረሰ ያለውን አደጋ፣ የንብረት ውድመትና ዝርፊያውን መንግሥት በአፋጣኝ ሊያስቆመው እንደሚገባም አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ኮሚሽነር ጀማል መሐመድ በበኩላቸው በክልሉ ጅግጅጋ ከተማ የተከሰተው ብጥብጥ ሱቆች ላይ ዘረፋ መፈጸሙንና ቤተክርስቲያን መቃጠሉን ገልጸዋል። በተከሰተው ችግር ምክንያት ዜጎች ፍርሃት ውስጥ እንደገቡና በዜጎች ላይ ማስፈራራት እየደረሰ እንደሆነ ጠቁመዋል። ማንም ዜጋ፣ ጎሳና ሃይማኖት ሳይለየው በአገሩ ውስጥ ተንቀሳቅሶ የመኖር መብት እንዳለው ገልጸው እየተፈጸመ ያለው ተግባር ህገ ወጥ ስለሆነ በአስቸኳይ መቆም አለበት ብለዋል። በሁከትና ብጥብጡ ምክንያት የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ ሶማሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ባልታወቁ ሰዎች መቃጠሉንና በጽህፈት ቤቱ ያሉ የምርመራ ሰነዶች መቃጠላቸውንና መዘረፋቸውን ጠቅሰዋል። በተጨማሪም የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የተወሰኑ ሰራተኞች በከፍተኛ ሁኔታ ድብደባ እንደደረሰባቸውና በአሁኑ ሰአት ሁሉም ሰራተኞች ራሳቸውን ለመጠበቅ ተደብቀው እንደሚገኙም አስረድተዋል። የኮሚሽኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ላይ አደጋ መድረሱ ከዚህ በፊት በክልሉ የሚገኙ የአገር ሽማግሌዎች በክልላቸው አንዳንድ አካባቢዎች እየተፈጸመ ያለውን ሰብአዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ ለዋና ኮሚሽነር ያቀረቡትን ቅሬታ ተከትሎ እየተደረገ ያለውን ምርመራ ለማደናቀፍ እንደሆነ ነው ኮሚሽነር ጀማል የተናገሩት። የክልሉ መንግስት የክልሉ የጸጥታ ሃይል አስፈላጊውን ጥበቃ ለሰራተኞቹ እንዲያደርግ መጠየቁን አመልክተዋል። የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ለዋናው ኮሚሽነር ጉዳዩን አስመልክቶ ሪፖርት ማድረጉንና ኮሚሽነሩ ከክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ መሐመድ ረሺድ ጋር መወያየታቸውን ጠቁመዋል። በክልሉ እየተፈጸመ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በማጣራት ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች ላይ ከዚህ በፊት ማስፈራሪያና ስራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ ጫና እየደረሰባቸው እንዳለም አብራርተዋል። ከምርመራው ጋር በተያያዘ ድብደባ ተፈጽሞባቸው ጉዳት ደርሶባቸው እንደነበር አስታውሰው የክልሉ መንግስት እስካሁን ጉዳዩን አጣርቶ ተጠያቂውን አካል ለህግ እንደሚያቀርብና በይፋ ኮሚሽኑን ይቅርታ እንደሚጠይቅ ገልጾ የነበረ ቢሆንም ይህንንም እስካሁን እንዳላደረገ አብራርተዋል። በክልሉ የሚገኘው የኮሚሽኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ጅግጅጋ ከተማን ጨምሮ በደጋሀቡር፣ ቀብሪደሀርና ጎዴ አካባቢዎች የተነሱት የሰብአዊ መብት ጥሰት ጉዳዮች ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አክለዋል።