አዲሱ ስርአተ ትምህርት በግብርናው ዘርፍና በአረንጓዴ ልማት ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ነው- ትምህርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ ስርአተ ትምህርት በግብርናው ዘርፍና በአረንጓዴ ልማት ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ነው- ትምህርት ሚኒስቴር
ሀምሌ 1/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አዲሱ ስርአተ ትምህርት በግብርናው ዘርፍ እንዲሁም በአረንጓዴ ልማት ለውጥ ማምጣት የሚያስችል መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ገለጹ።
ሚኒስትሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት አዲሱ ስርአተ ትምህርት ለግብርና እና አረንጓዴ ልማት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ነው።
በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስራ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ስርአተ ትምህርቱ ትኩረት ያደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።
ግብርና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ እስክ ቀጠለ ድረስ አዲሱ ትውልድ ስለ ግብርናና አካባቢ ጥበቃ በቂ እውቀት እንዲኖረው ያስፈልጋል ብለዋል ሚኒስትሩ።
በትምህርት ቤቶች ወጣቶች በዘርፉ ትምህረት እያገኙ በተግባርም እየተሳተፉ ማስቀጠል ተገቢ መሆኑን አብራርተዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ የሁሉንም ማህበረሰብ ተሳትፎ የሚጠይቅ ሁለንተናዊ ተግባር ስለመሆኑም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
በአምቦ ዮኒቨርስቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ብዙነሽ ሚዴክሳ በበኩላቸው የግብርና ልማትና የተፈጥ ሃብት ጥበቃ የዜጎች ሁሉ ግደታ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ የአረንጓደ ልማት እየተከናወነ ቢሆንም በአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ግን ብዙ መስራትን ይጠይቃል ነው ያሉት።
የፋብሪካ ፍሳሽ አወጋገድ፣ የፕላስቲክና መሰል በአፈርና አካባቢ ላይ ብክለት የሚያመጡ ቆሻሻዎችን የአወጋገድ ስራ ላይ ለውጥ ማምጣት ለነገ የሚተው መሆን የለበትም ብለዋል።
ለዚህም የትምህርት ተቋማት፣ ባለደርሻ አካላት፣ ዜጎችና የዘርፉ ተመራማሪዎች ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
በአካባቢ ጥበቃ ላይ ለውጥ ለማምጣት በተለይ የትምህርት ተቋማት ትልቁን ድርሻ መውሰድ ይገባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።
የአምቦ ዩኒቨርስቲ በዘርፉ ጥናትና ምርምር በማድረግ ማህበረሰቡን እየደገፈ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ስርዓተ ትምህርት በትምህርትና ስልጠና ሥርዓት ውስጥ የሚገኙ መርሃ ግብሮችን የሚመራ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑ ይነገራል።
የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ እንዲሁም የጥናትና ምርምር ስራዎች የስርአተ ትምህርት አይነተኛ ትኩረቶች መሆናቸውም ይታወቃል።