ቀጥታ፡

በአሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ለተፈናቀሉ ዜጎች ያዘጋጁት የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን የፊታችን እሁድ ይካሄዳል

ሀምሌ 1/2013 (ኢዜአ) በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ዜጎች ያዘጋጁት የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን በመጪው ሐምሌ 4 ቀን 2013  እንደሚከናወን ተገለጸ።

"የሶስት ሺህ ለጋሾች አሻራ ቴሌቶን" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው መርሃ ግብር በበይነ መረብ አማካኝነት የሚካሄድ ነው።

ቴሌቶኑ በዋሺንግተን ዲሲ የሰዓት አቆጠጣር 10:00 pm ወይም በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ ይከናወናል።

የቴሌቶን ገቢ ማሰባሰቢያው የተፈናቀሉ ዜጎች የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ አላማ ያለው መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሰላም ጓድ ዋና ፀሐፊ አቶ ደምለው አልማው ለኢዜአ ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ በመላው ዓለም የሚገኙ ዳያስፖራዎች፣ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በቴሌቶኑ የሚሰበሰበው ገንዘብ በመጠለያዎች ለሚገኙ ዜጎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስና ብርድ ልብስ በመግዛት ድጋፍ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ተፈናቃዮች ለችግር እንዳይጋለጡ ድጋፍ ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ነው አቶ ደምለው ያስረዱት።

የኢትዮጵ ዳያስፖራ ሰላም ጓድ 12 አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን ሐምሌ 9 ቀን 2013 ዓ.ም ከአሜሪካ በመነሳት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣና የ14 ቀናት ቆይታ ለማድረግ እቅድ መያዙን ገልጸዋል።

ቡድኑ በኢትዮጵያ በሚኖረው ቆይታ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የተፈናቀሉ ዜጎችን ይጎበኛሉ፤ እንዲሁም ድጋፉን ያደርሳሉ።

የልዑካን ቡድኑ ዜጎቹ ያሉበትን ሁኔታ በመመልከት ወደ አሜሪካ ሲመለስ ዳያስፖራው ያሉበትን ሁኔታ የማሳወቅና ግልጽ የሆነ አረዳድ እንዲኖረው የማድረግ ተግባር ይከናወናል ብለዋል።

ዳያስፖራው ወገኖቹ ያሉበትን ሁኔታ ማስረዳት ከተቻለ ትርጉም ያለው ድጋፍ ለማሰባሰብና ተፈናቃዮች በዘላቂነት ለመደገፍ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

"ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች የተፈናቀሉ ዜጎች በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት" በሚል የሚያሰራጯቸውን መረጃ ለማጣራት ዳያስፖራው መሬት ላይ ያለውን እውነታ መረዳት አለበት ጉብኝቱ ከዚህ አንጻር የራሱ ፋይዳ አለው ነው ያሉት አቶ ደምለው።

የልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያና በዳያስፖራው መካከል ትስስር በመፍጠር ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የወገኑን ችግር የሚካፈልበትና ሸክሙን የሚጋራበት ሁኔታ ማመቻቸት አላማ አለው።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሰላም ጓድ በረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ በሰላም ግንባታና እርቀ ሰላም ላይ ለመስራት እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል እቶ ደምለው።

ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የኖሩባቸውን እሴቶች በአሁኑ ሰዓት እየተሸረሸሩ ነው ያሉት አቶ ደምለው እነዚህ እሴቶች የሚፈጠሩ ችግሮች ሕዝቡ በራሱ የሚፈታባቸው መንገዶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

"እሴቶቹ እየተሸረሸሩና ችላ እየተባሉ መምጣታቸው የውጪ አገራት የኢትዮጵያ ችግር ፈቺ እኛ ነን ብለው መፍትሔ አቅራቢ እንዲሆኑ በር ከፍቶላቸዋል" ነው ያሉት አቶ አልማው።

ኢትዮጵያውያን ዳግም የእሴቶቻቸው ባለቤት በመሆን የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በራሳቸው መፍታት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት ጉዳይ ለመንግስትና ለፖለቲከኞች የሚተው ሳይሆን ዋነኛ የሰላሙ አምጪ ሕዝቡ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሰላም ጓድ በኢትዮጵያ ሰላምና እድገት እንዲመጣ ከመንግስትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት መስራት እንደሚፈልግም ነው አቶ ደምለው የገለጹት።

በተጨማሪም ስብስቡ የኢትዮጵያ ጥቅምና ክብር በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ የተሟጋችነት (Advocacy) ስራዎች እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

አሜሪካና ሌሎች የውጪ አገራት በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት "እንዘዝ" የሚሉት በድህነታችንና በጠባቂነታችን ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

ከድህነት ለመላቀቅ ጠንክሮ መስራት እንደሚያስፈልግና ይሄ መሆን ሲችል ኢትዮጵያ በተሻለ መልኩ ብሔራዊ ክብሯንና ጥቅሟን ማስጠበቅ እንደምትችል አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሰላም ጓድ በሚያዚያ ወር 2013 ዓ.ም በአሜሪካ ከሚገኙ 10 የሲቪክ ማህረሰብ ድርጅቶችና ምሁራን አማካኝነት የተቋቋመ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም