ቀጥታ፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን በመኸሩ ከሚለማው ከግማሽ በላይ የሚሆነው ማሳ በኩታ ገጠም ይለማል--

ደብረ ማርቆስ ፤ ሐምሌ 01/2013 (ኢዜአ) በምስራቅ ጎጃም ዞን በመኸር ወቅት በዘር ከሚሸፈነውን መሬት 604 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በኩታገጠም እንደሚለማ የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።

ምስራቅ ጎጃምን ጨምሮ በአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች የኩታ ገጠም አሰራርን በማዳበር  በምርት ዘመኑ ከአራት ሚሊዮን 500ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በሰብል ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተመልክቷል።

በዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ  አቶ አባበው እንየው  ለኢዜአ  እንደተናገሩት፤ አዳዲስ የግብና አሰራሮችን ወደ  አርሶ አደሩ ለማውረድም  በየደረጃው  ላሉ የግብርና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቶ ተሰማርተዋል።

በዚህም በመኸር ወቅት እርሻ በዘር ከሚሸፈነው መሬት ውስጥ 357  ሺህ 816  ሄክታር  የሚሆነውን ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በመጠቀም ጤፍ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ የቢራ ገብስ፣ ቦለቄ እና ስንዴ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢው የሚጥለው ዝናብ ዘግይቶ ቢጀምርም እስካሁን በኩታ ገጠም ለማልማት  ከታሰበው ውስጥ ከ72ሺህ በላይ የሚሆነውን በዘር መሸፈኑን አስረድተዋል።

በምርት ዘመኑ ከ980 ሄክታር በላይ በሚሆነው መሬት ላይ የዘር ስራውን በትራክተር ታግዞ እንደሚከናወንም ጠቅሰዋል።

ባለሙያው እንዳሉት፤ በኩታ ገጠም መዝራት አረምን በጋራ ለማረም፣ ተባይን በቀላሉ ለመከላከል፣ ለሰብሉ ተገቢ እንክብካቤ ለማድረግና ምርቱ ሲደርስ በኮምባይነር ታግዞ ለመሰብሰብ ያለውን ፋይዳ አርሶ አደሩ ተገንዝቧል።

በዞኑ ደብረ ኤሊያስ ወረዳ የጉፍጭማ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሽመልስ ገዳሙ በሰጡት አስተያየት፤ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ  አዳዲስ አሰራሮችን ከግብርና  ባለሙያዎች ትምህርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ስንዴ እና በቆሎ በኩታገጠም ዘርተው በጋራ መንከባከብ በመቻላቸው የጠበቁትን ምርት ማግኘታቸውን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅትም  ከአንድ ሄክታር በሚበልጥ ኩታ ገጠም ማሳቸው ላይ በቆሎ  መዝራታቸውን  አስረድተዋል።

ከግማሽ ሄክታር በላይ የሚሆን ማሳቸውን በኩታ ገጠም ለማልማት ዘር መዝራታቸውን  የገለጹት ደግሞ በአነደድ ወረዳ የወቢ እነችፎ ቀበሌ አርሶ አደር ተዋቸው አጥናፍ ናቸው።

"ባለፈው ዓመት በኩታ ገጠም ካለማሁት ጤፍ እና ስንዴ ያገኘሁት ምርት በፊት አገኝ ከነበረው በሄክታር የስድስት ኩንታል ምርት ጭማሪ ስላለው ዘንድሮም በኩታ ገጠም አለማለሁ" ብለዋል።

በምስርቃ ጎጃም ዞነ በመኸር እርሻው በዘር ከሚሸፈነው መሬት ከ21  ሚሊዮን ኩንታል  በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ  እየተሰራ መሆኑን ከመምሪያው የተገኘው  መረጃ  ያመላክታል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በልማትና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰኔ 29/2013ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት፤ በክልሉ በመኸሩ ወቅት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በግብአትነት የሚያገለግል 7 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩና በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ተሰራጭቷል።

በምርት ዘመኑ የእርሻ ስራ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን በማዳበር አረምን ለማስወገድና ተባይን ለመከላከል በጋራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በምርት ዘመኑ  ከአራት ሚሊዮን 500ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በሰብል ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ዜና አገልገሎት በወቅቱ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም