ቀጥታ፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአፍሪካ ህብረት የሚካሄደው ድርድር ተገቢ መፍትሄ መሆኑን የናይል ተፋሰስ አገራት ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2013(ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአፍሪካ ህብረት የሚካሄደው ድርድር ተገቢ መፍትሄ መሆኑን የናይል ተፋሰስ አገራት ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የናይል ተፋሰስ አገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በግድቡ ወቅታዊ የድርድር ሂደት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህ ወቅት እንዳሉት የናይልን ወንዝ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት በማይጎዳ መልኩ ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ በጋራ መጠቀምና ማልማት ይቻላል።

ይሁን እንጂ ግብጽና ሱዳን ጉዳዩ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት እንዲሄድና ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ማድረጋቸው ተገቢ አይደለም ብለዋል።

በመሆኑም ከዚህ አካሄድ በመውጣት የአፍሪካን ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው መርህ መፍታት እንደሚገባ ገልጸው፤ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት መካሄዱም ተገቢ መፍትሄ የሚያመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የታላቁን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ በጸጥታው ምክር ቤት ግዴታ ውስጥ እንደማትገባ የገለጹት አቶ ደመቀ፤ በአፍሪካ ህብረት የተጀመረው ድርድር የተሻለ መፍትሄ መሆኑን ኢትዮጵያ ታምናለች ብለዋል።

በመሆኑም የታችኛው ተፋሰስ አገራት የአፍሪካ ህብረትን ሚና በማጣጣል የቅኝ ግዛት ስምምነት ለመተግበር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ መቃወም እንዳለባቸው አሳሰበዋል።

የላይኛው የተፋሰስ አገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶችም ኢትዮጵያ የላይኛው ተፋሰስ አገራት የግድቡ ዋነኛ ባለድርሻ አካላት መሆናቸውን በመገንዘብ ያደረገችውን ወቅታዊ ማብራሪያ አድንቀዋል።

በናይል ተፋሰስ የመጠቀምና የመልማት ሂደት  የጋራ ጉዳያችን በመሆኑ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  "የጋራ ጉዳያችን ነው" ብለዋል።  

የአፍሪካዊያንን ችግር በአፍሪካውያን መፍታት የሚበረታታ በመሆኑ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድርም በአፍሪካ ህብረት ማለቅ አለበት ነው ያሉት።

በድርድሩ ሰላማዊ መፍትሄ መፈለግ እንዳለባቸውና የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ጣለቃ የመግባት ስልጣን እንደሌለውም ገልጸል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም