ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በበጀት አመቱ ከ42 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መስብሰቡን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30/2013 ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2013 በጀት አመት ከ42 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ፤ የበጀት አመቱን ገቢ አፈፃፃምንና የቀጣዩን ዓመት እቅድ በሚመለከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም በ2013 በጀት ዓመት 42 ቢሊዮን 479 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

የተሰበሰበው ገቢ በበጀት ዓመቱ ታቅዶ የነበረውን ሙሉ በሙሉ ማሳካቱንም ተናግረዋል።

ለግብር ከፋዮች የላቀ አገልግሎት መስጠት መቻሉ፣ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎች በመስራቱና፣ ግብር ከፋዮች የህግ ተገዥ እንዲሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ መስራት በመቻሉ ገቢው መሳካቱን ጠቅሰዋል።

ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጀት በመሰራቱና ግብር ከፋዮችም መክፈል የሚገባቸውን ግብር በወቅቱ ማሳወቃቸውና በመክፈላቸው መሆኑንም አብራርተዋል።

በኮሮናቫይረስ  መከሰት ሳቢያ ገቢያቸው ለቀነሰባቸው 6 ሺህ 700 ግብር ከፋዮች የግብር ምህረት በማድረግ ስራቸውን እንዲቀጥሉ መደረጉንም ሃላፊው ገልጸዋል።

ቢሮው ግብር ከመሰብስብ ባለፈም ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት በበዓላት ጊዜ ለአቅመ ደካሞች የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉን አስታውሰዋል።

በአሰራር ሂደት የስነ ምግባር ጉድለት የታየባቸው 80  የቢሮው ሰራተኞች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉንም አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል።

እንደ ሃላፊው ገለፃ በክረምቱ 20 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ በተያዘው እቅድ መሰረት ከሀምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ስራው ይጀመራል።

በዚህም ሁሉም ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በወቅቱ በመክፈል አገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ በሚቀጥለው በ2014 በጀት አመት ከ48 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ማቀዱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም