ቀጥታ፡

ቼክ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደውን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በአዎንታዊነት ትቀበላለች - አምባሳደር ፓቬል ማይክስ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) ቼክ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ በአዎንታዊ መልኩ እንደምትመለከተው በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ፓቬል ማይክስ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምሳደር ፓቬል ማይክስ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ ያደረገው የተናጠል የተኩሰ አቁም በአዎንታ የሚታይ ነው።

ይህም በትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በግጭቱ ምክንያት በተለይም በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ሰብዓዊ ቀውስ ለማስቆም ያስችላል ብለዋል።

መንግሥት የወሰደው የተናጠል የተኩሰ አቁም በሁሉም አካላት ተቀባይነት እንደሚኖረው በአግባቡ ገቢራዊ እንደሚሆን ያላቸውንም እምነት ገልጸዋል።

በጉዳዩም ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን አምባሳደር ፓሼል ተናግረዋል።     

በሌላ በኩል ኢትዮጵያና ቼክ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ታሪካዊና ፈርጀ ብዙ ግንኙነት ያላቸው አገራት መሆናቸውንም አምባሳደር ፓሼል ገልጸዋል።

ግንኙነታቸው የመንግሥታት ብቻ ሳይሆን በኅዝብ ለኅዝብ ግንኙነትም የዳበረ መሆኑን ጠቁመዋል።  

ለአብነትም ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ በተወረረችበት ወቅት አገራቸው ለኢትዮጵያ ነጻነት ትግል ድጋፍ ማድረጓን በማንሳት።  

አገራቸው በጤናው ዘርፍም ከኢትዮጵያ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላት ገልጸው የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ እያደረገች መሆኗን ጠቁመዋል።

በቅርቡም 20 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው ለህክምና የሚውሉ ኦክስጅኖችን ድጋፍ ለማድረግ በሂደት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የተለያዩ የግብርናና እሴት የተጨመረባቸው የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች በቼክ ሪፐብሊክ ከፍተኛ የገበያ እድል እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ኤምባሲው ሠራተኞች ላለፉት ሦስት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ተሳታፊ በመሆን ከ1 ሺህ በላይ ችግኝ መትከላቸውን ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለትም በኤምባሲው አዲሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ 300 ችግኞችን ተክልዋል።

እስካሁንም ከውጭ የተገተኙ እጽዋቶችን ጨምሮ እንደ ኮሶ፣ ጊርጊራ፣ ጥድ፣ ወይራና ሌሎችንም አገር በቀል የሆኑ የእጽዋት ዝርያዎችን መተከላቸውን ተናግረዋል።

ችግኞቹም በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በደቡብ ኦሞ፣ ምንጃር ሸንኮራና ሌሎችም የአገሪቱ አከባቢዎች በመሄድ መትከላቸውን አምባሳደሩ ጠቁመዋል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩም ነው አምባሳደር ፓቬል ያረጋገጡት።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም