በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላና እንክብካቤ ላይ መረባረብ ይገባል--- ዶክተር ተመስገን ቡርቃ - ኢዜአ አማርኛ
በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላና እንክብካቤ ላይ መረባረብ ይገባል--- ዶክተር ተመስገን ቡርቃ
ድሬዳዋ፤ ሰኔ 30/2013 (ኢዜአ) ከሀገሪቱ ወንዞች ዘላቂ ጥቅም ለማግኘት በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላና እንክብካቤ ላይ መረባረብ እንደሚገባ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ተመስገን ቡርቃ አሳሰቡ፡፡
በድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የተመራ የካቢኔ አባላት፣ የከተማና ገጠር አመራሮች ቡድን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በድሬዳዋ ከተማ አካሂዷል፡፡
የማዕከሉ አስተባባሪ በወቅቱ እንዳሉት፤ ዘንድሮ በሀገሪቱ የሚተከሉ ችግኞች የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመተግበርና ወንዞች ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ ያደርጋል፡፡
በዘንድሮው መርሃ ግብር የጥላና ፍራፍሬ ችግኞችን በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጭምር በመትከል የአረንጓዴ ልማት ዘመቻው የጋራ አጀንዳ ለማድረግ እንደሚረዳ አመልክተዋል፡፡
''ይህ ተግባር የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ሁለንተናዊ ትስስር ከፍ ለማድረግ ያግዛል'' ብለዋል፡፡
ችግኝን መትከል ቀዳሚ ቢሆንም መንከባከብና ማሳደግ ላይ መረባረብ እንደሚገባ ዶክተር ተመስገን አሳስበዋል፡፡
ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ቡህ በበኩላቸው፤ ችግኞችን መትከልና መንከባከብ የድሬዳዋን ሞቃታማ አየር ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግና በየጊዜው በከተማዋ ላይ የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
አስተዳደሩ ለጅቡቲ ከ200 ሺህ በላይ ችግኞች በማቅረብ ግንኙነታቸውን በአረንጓዴ ልማትም እንደሚያስተሳስርና ሁሉን አቀፍ ግንኙነታቸውን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡
በአስተዳደሩ ከሚተከሉት ሁለት ሚሊዮን የፍራፍሬና ጥላ ችግኞችን ለመትከል ወደ ተግባር መገባቱን የተናገሩት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ናቸው፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር ፤በየጊዜው የሚተከሉ ችግኖች መላልሶ መንከባከብና መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
በተለይ አመራሩ በኢንዱስትሪ መንደር አጠገብ የተከላቸው ችግኞች ብክለትን በመከላከል ለሥራ ምቹ ሁኔታን ስለሚፈጥሩ ልዩ እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል፡፡
በአስተዳደሩ በሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተተከሉት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ 68 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን የግብርና ቢሮው መረጃ ያመለክታል፡፡
ዘንድሮ በሀገር ደረጃ ''ኢትዮጵያን እናልብሳት'' በሚል የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እየተካሄደ ሲሆን በጎረቤት ሀገራት ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል፡፡