ቀጥታ፡

ከአገራችን ብንወጣም ኢትዮጵያ ከልባችን አትወጣም፤ ለአገራችን በያለንበት አምባሳደሮች ሆነን እናገለግላለን- ዳያስፖራዎች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30/2013 (ኢዜአ) ከአገራችን ብንወጣም ኢትዮጵያ ከልባችን አትወጣም፤ ለአገራችን በያለንበት አምባሳደሮች ሆነን እናገለግላለን ሲሉ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገለጹ።

"ዳያስፖራው ከአገር ቢወጣም ኢትዮጵያ ከልቡ አልወጣችም በአገሩ ጉዳይ ላይ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እየተወጣ ነው፤ ይህንንም አጠናክሮ ይቀጥላል" ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል።

ነዋሪነታቸውን በእንግሊዝ ለንደን ያደረጉትና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ተግባር ምክር ቤት የሚዲያ ክፍል ሃላፊ አቶ አለባቸው ደሳለኝ "እኛ ከአገራችን ብንወጣም ኢትዮጵያ ከልባችን አትወጣም፤ ለአገራችን በያለንበት አምባሳደሮች ሆነን እናገለግላለን፤ ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ሕዝብ እድገትና ልማት ነው" የሚፈልገው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች የጀመረቻቸውን ስራዎች ዳያስፖራው ባለው አቅም እየደገፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲሁም በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖችና ለአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ዳያስፖራው ኢትዮጵያ በውጪ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት እየደረሳባት ያለውን ጫና የመመከት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት አካባቢ የሚገኙ የፓርማላ (የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት) አባላት ላይ ተጽእኖ የሚያደርጉ ግለሰቦችን (ሎቢስቶችን) በመቅጠርና በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ዘመቻ በማድረግ በተደራጀ መልኩ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

"በውጪ አገር የሚገኙ የሕወሓት ቡድን ደጋፊዎች በትግራይ ክልል ያለውን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚያስተላልፋቸውን ሐሰተኛና የተዛቡ መረጃዎች በማጋለጥ ትክክለኛውን መረጃ እየሰጡ ነው" ብለዋል አቶ አለባቸው።

በምርጫው ስልጣን የሚይዘው መንግስት ሕዝቡ በድምጹ የሰጠውን አደራ ተቀብሎ ኢትዮጵያን የማሻገር እንዲሁም ሉዓላዊነቷንና አንድነቷን የማስጠበቅ ሃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል።

መንግስትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተግባብተው የሚሰሩበት የጋራ እሳቤ ሊኖራቸው እንደሚገባም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩነቱን ወደ ጎን በመተው ኢትዮጵያን ከጠላቶቿ የመጠበቅና አንድነታቸውን ማጥበቅ እንዳለባቸው አክለዋል።

በአሜሪካ ነዋሪነታቸውን ያደረጉትና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ተግባር ምክር ቤት ጊዜያዊ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አለማየሁ ስለሺ ዳያስፖራው የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች ጋር በይነ መረብ በአካል ውይይት በማድረግ ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ጫና እንዲቆም ግፊት እያደረጉ ነው ብለዋል።

"ኢትዮጵያን ሲቪክ ካውንስል" የሚል ስያሜ ያለው ድርጅት የፓርማላ (የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት) አባላት ላይ ተጽእኖ የሚያደርጉ ግለሰቦችን (ሎቢስቶችን) በመቅጠር ባለስልጣናትን የማግባባት ስራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በትግራይና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ በአረብ አገራትና በምዕራባውያን የሚደርሱትን ጫናዎች ዳያስፖራው በመመከት የኢትዮጵያን ክብር ለማስጠበቅ እየታገለ መሆኑን ተናግረዋል።

"ወቅቱ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ዘመን ነው ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና እየመጣች ነው" ያሉት አቶ አለማየሁ ለዘመናት ሲቆዘምበት የነበረው የአባይ ወንዝ በሕዳሴ ግድብ አማካኝነት ታሪኩን ቀይሮ ለኢትዮጵያ ተስፋ ሰጥቷል ብለዋል።

"ኢትዮጵያውያን ኩሩ ሕዝቦች ናቸው በነጻነታቸው የማይደራደሩ የውጪ ሃይሎችን ጣልቃ ገብነት ለዘመናት ያልተቀበለ አንደነቱን ያስጠበቀ ሕዝብ ነው" ብለዋል አቶ አለማየሁ።

አሁንም ኢትዮጵያውያን ያልተጨበጡ ወሬዎችን፣ አሉባልታዎችና ሐሰተኛ መረጃዎችን ከማሰራጨት በመቆጠብ ለኢትዮጵያ አንድነት ጠበቃ መሆን አለባቸው ብለዋል።

"ዳያስፖራው ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያን ለማገዝ ቆርጦ ተነስቷል" ያሉት አቶ አለማየሁ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና በሌሎች አገራዊ ስራዎች ላይ ድጋፉን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

መንግስት በአሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች የሕዳሴ ግድቡን ቦንድ ለመግዛት የሚያስችላቸውን አሰራር ቀላል የሚያደርግበትን ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት አክለዋል።

ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ስም ለማጠልሸት የሚሰሩ ቡድኖችን እንቅስቃሴ በመመከት የአገሪቷን መልካም ገጽታ የማስተዋወቅ ስራ እያከናወነ ይገኛል ያሉት ደግሞ በአሜሪካ ነዋሪ የሆኑትና በዋሺንግተን ዲሲ የሰላምና አንድነት ግብረ ሃይል የኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ጣሰው መልዐከ ሕይወት ናቸው።

በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለኮንግረስ አባላት፣ ለሴናተሮችና ለባለስልጣናት ሃሳባቸውን የሚገልጹበት "ወተር ቮይስ" የሚባል ስርዓት መዘርጋቱን አመልክተዋል።

በአሜሪካ በዳያስፖራው የተቋቋሙ የተለያዩ ቡድኖች በጋራ እየሰሩ መሆናቸው የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለመገንባት ለሚደረገው እንቅስቃሴ ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል።

"የሕወሓት የዲጂታል ቡድን በትግራይ ክልል የተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ አስመለክቶ የሚያሰራጨውን ፕሮፓጋንዳ ትክክል አለመሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስረዳት ተግባር እያከናወነ ይገኛል" ብለዋል አስተባባሪው።

ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የዜግነትና የትውልድ ሃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነና ይሄም ተግባር ወደፊትም እንደሚጠቀጥል ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢያ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበራቸው ቆይታ ለዳያስፖራው የሰጡት እውቅና ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ምስጋናቸውን አቅርበው፤ እውቅናው ለዳያስፖራው ጥሩ የሞራል ድጋፍና ብርታት እንደሆነና የመንግስት ድጋፍ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም