የብዙዎቹ እናት አበበች ጎበና በችግር ውስጥ ላሉ ህጻናት የመኖር ምክንያት በመሆን ህያው ስራን ትተውልን አልፈዋል ---ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የብዙዎቹ እናት አበበች ጎበና በችግር ውስጥ ላሉ ህጻናት የመኖር ምክንያት በመሆን ህያው ስራን ትተውልን አልፈዋል ---ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29 ቀን 2013 (ኢዜአ) የብዙዎቹ እናት አበበች ጎበና በችግር ውስጥ ላሉ ህጻናት የመኖር ምክንያት በመሆን ህያው ስራን ትተውልን አልፈዋል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
የክብርት አበበች ጎበና ስርአተ ቀብራቸው በአዲስ አበባ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ተከናውኗል።
በቀብር ስነ ስርዓቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ፓትርያሪክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል፡፡
ምክትል ከንቲባዋ በዚህን ወቅት የክብርት ዶክተር አበበች ጎበና ህልፈተ ህይወት የመላው ኢትዮጵያውያን ሀዘን መሆኑን ገልጸዋል።
እርሳቸውን በሞት ብናጣም የመንፈስ ጥንካሬያቸው ሁሌም አብሮን ይኖራልም ነው ያሉት።
ለሰዎች መኖርን፣ ለችግረኞች መራራትንና ጠያቂ የሌላቸውን መደገፍን ከእርሳቸው ተምረናል ብለዋል።
ለበርካታ ህጻናት የመኖር ምክንያት በመሆንም ዘላለም የሚወሳ ህያው ስራ ስርተዋል ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፤ ህልፈታቸው መራር ቢሆንም አርአያ በሆነ ስራቸው እንጽናናለን ብለዋል።
ክብርት ዶክተር አበበች ጎበና ባደረባቸው ህመም ሳቢያ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሰኔ 27 ቀን 2013 ዓ.ም በተለወዱ በ85 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል።