ቀጥታ፡

በመተከል ዞን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል የሚያስችል የምክክር መድረክ ተካሄደ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29 ቀን 2013 (ኢዜአ) በመተከል ዞን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል የሚያስችል የምክክር መድረክ ተካሄደ። 

በመተከልና አጎራባች አካባቢዎች የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ተገልጿል። 


በመተከል ዞን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል በሚቻልባቸው የእቅድ ስራዎች ዙሪያ ከአማራ ክልል አዊ ዞንና ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን አጎራባች የወረዳዎች የጸጥታ አመራርና የስራ ኃላፊዎች ምክክር አድርገዋል።


ህገ-ወጥ የመሳሪያ ዝውውር፣ የመሬት ወረራ፣ በህገወጥ መንገድ መታወቂያ ማደል፣ የከብት ዝርፊያ እና ሌሎች ተያያዥ ህገወጥ ተግባራት ለቀጠናው ስጋት እየሆኑ መምጣታቸው ተነስቷል።


ችግሩን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከወረዳ እስከ ቀበሌ አደረጃጀቶችን በማጠናከር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን አጠናክሮ በተለያዩ የልማትና የግብይት ስራዎች ማስተሳሰር እንደሚገባ ተገልጿል። 


ህብረተሰቡን ለሞትና መፈናቀል የሚዳርጉ አካላትን በመለየት በህግ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባም ተጠቁሟል።


የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ፤ በሁለቱ ክልሎች በነዋሪዎች መካከል ያለው የሰላም ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት ከወረዳ እስከ ቀበሌ ያሉ አደረጃጀቶችን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም መስራት ይገባል ብለዋል።


የጸጥታ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ህብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዲኖር በማድረግ ለግጭትና የሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ነገሮችን ማስቆም እንደሚገባም ገልጸዋል።


የአዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባይነሳኝ ዘሪሁን፤ የቀጠናውን ሰላም የሚያደናቅፉ የጸጥታ ስጋቶችን ለይቶ የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር የምክክር መድረኩ ዋነኛ ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል።


በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራትን በማስቀመጥ ማን ምን እና እንዴት ይስራ የሚለውን እድል በመፍጠር የስራ ድርሻ መውሰድ እንደሚገባም አንስተዋል።


የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ፤ የእርቅ መድረኮችን መፍጠርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም