የኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት ከሃምሌ ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት ከሃምሌ ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል
አዲስ አበባ ሰኔ29/2013(ኢዜአ)የመንግሥት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት ከሀምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ መሆን የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።
ኤጀንሲው በግዥ ሥርዓቱ አተገባበር ዙሪያ ለአቅራቢዎችና ማህበራት ገለጻ አድርጓል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ፤ የኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ባለፈው ዓመት ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አንስተዋል።
ለተግባራዊነቱ መንግስት ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን አስፈላጊው መሰረተ ልማት ዝግጅት በማድረጉ ከሀምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በዘጠኝ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ በሙከራ ደረጃ ይጀመራል ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ ገቢዎች፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አጀንሲ፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በሙከራ ደረጃ የሚተገብርባቸው ተቋማት መካከል ናቸው።
በመስሪያ ቤቶቹ የሚወጡ ሁሉም ጨረታዎችና የጨረታ ሂደቶች ሙሉ በሙሉ በመንግሥት የኤሌክትሮኒክ ግዥ የሚፈጸም መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይም ከ6 ወራት በኋላ 50 የፌደራል ተቋማት በግዥ ስርዓቱ እንደሚታቀፉም ጠቁመዋል።
በሚቀጥሉት ዓመታት የኤሌክትሮኒክ አገልግሎቶችን ሽፋን አሁን ካለው 2 በመቶ ወደ 85 በመቶ ከፍ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል አቶ ሀጂ።
የኤሌክትሪኖክ ዘዴ ገዥና አቅራቢዎችን በኢንተርኔት የሚገበያዩበት ሲሆን አሰራሩ ብልሹ አሰራርንና ሙስናን ከመከላከል ባለፈ የግብይት ጊዜው እንዲያጥር ያደርጋል ነው ያሉት።
በተለይም የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚበጅተው ዓመታዊ በጀት ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው ለግዥ እንደሚውል ጠቅሰው አሰራሩ ቁጠባን የሚያሳድግ እንደሆነም አክለዋል።
የኤሌክትሮኒክ ግዥ አሰራር ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ በመንግስት ግዥ ስርዓት ውስጥ ክፍተቶችና ጉድለቶች እንዳይፈጠሩ፣ የጨረታ ተደራሽነትን ለማቀላጠፍ፣ ግልጽነትና ውድድር እንዲኖር የሚያስችል እንደሆነ ተጠቁሟል።
በግዥ ስርዓቱ ውስጥ የሰዎች ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር የሚያደርግ እንደሆነም ተገልጿል።