ቀጥታ፡

አባቶቻችን ያቆዩልንን ሀገር በእውቀትና ጥበብ ለተተኪው ትውልድ ማሸጋገር አለብን----ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስ

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2013(ኢዜአ) አባቶቻችን ያቆዩልንን ሀገር በእውቀትና ጥበብ ለተተኪው ትውልድ ማሸጋገር አለብን ሲሉ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስ ገለጹ።

ኮሚሽነሩ ይህን ያሉት የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 104 ተማሪዎች ባስመረቀበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ነው፡፡ 

ኮሚሽነሩ በዚሁ ወቅት ተመራቂዎቹ በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ ተግባር በማከናወን ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። 

ኢትዮጵያ ታላቅ የለውጥ ተስፋን አንግባ ወደ ብልጽግና እየተጓዘች ትገኛለች ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ተመራቂዎቹ የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ ከዳር እንዲደርስ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ከአካዳሚው ያገኙትን እውቀት በአግባቡ በመጠቀም "አባቶቻችን ያቆዩልንን ሀገር በእውቀትና ጥበብ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት አለባችሁ" ነው ያሉት።

የአካዳሚው ፕሬዘዳንት አቶ አወሉ አብዲ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ለማሻገር ብቃት ያላቸው አመራሮችን ማፍራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

አካዳሚው ይህንን ተልዕኮ በመወጣት ረገድ የበኩሉን ደርሻ እየተወጣ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

አካዳሚው ከዚህ ቀደም በአንድ ፓርቲ ዕርዮት የተቃኙ ሰልጣኞችን ማፍራት ላይ ትኩረት ያደርግ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ከአንድ ፓርቲና ጥቂት ቡድኖች ይልቅ ህዝብን የሚያገለግሉ አመራሮችን የማፍራት ቁመና ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

አካዳሚው የዓለም አቀፍ እይታን ባገናዘበ የትምህርት ስርዓት እየተመራ መሆኑንም እንዲሁ።

አካዳሚው በጥናትና ምርምር ታግዞ በአዲስ መልክ ከተደራጀ በኋላ በበርካታ የትምህርት ዘርፎች ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝም አቶ አወሉ ጨምረው ገልጸዋል። 

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ከአፍሪካ ሀገራት ለሚመጡ ሰልጣኞች አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱንም ነው የተናገሩት።

የአካዳሚው ሬጅስተራር ኃላፊ ዶክተር ኃይለሚካኤል ተስፋዬ በበኩላቸው አካዳሚው በዛሬው ዕለት በአምስት ትምህርት ዘርፎች 104 ሰልጣኞችን ማስመረቁን ገልጸዋል፡፡ 

ተመራቂዎቹ በአመራር፣ በፐብሊክ ፖሊሲ፣ በልማታዊ ተግባቦትና ሚዲያ፣ በፌደራሊዝም ጥናት እንዲሁም በሰላምና ግጭት አፈታት ትምህርታቸውን የተከታተሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ተመራቂዎቹ በአካዳሚው ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀትና ልምድ ለሀገር ግንባታ ማዋል እንዳለባቸውም ነው ጥሪ ያቀረቡት።

ተመራቂዎቹ በበኩላቸው በቆይታቸው በቂ እውቀት መቅሰማቸውን ገልጸው፤ በዚህም ሀገራቸውን በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም