ቀጥታ፡

የአፍሪካ ወጣቶች እምቅ አቅማቸውን በሳይንሳዊ መንገድ ከተጠቀሙ ለቀጠናው ሰላም ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል- ሙፈሪያት ካሚል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29/2013(ኢዜአ) የአፍሪካ ወጣቶች እምቅ አቅማቸውን በሳይንሳዊ መንገድ ከተጠቀሙ ለቀጠናው ሰላም ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ።

የምሥራቅ አፍሪካ የተጠባባቂ ኃይል የወጣቶች ሥልጠና በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ይገኛል።

የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ አሥር አባል አገራት የተውጣጡ አባላት ያሉት ሲሆን ወጣቶች በአካባቢያዊና ቀጠናዊ ሰላምና ደህንነት ላይ እንዲሰሩ የተቋቋመ ነው።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፤ የአፍሪካ ወጣቶች እምቅ አቅማቸውን በሳይንሳዊ መንገድ ከተጠቀሙ ለቀጠናው ሰላም ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል።

የወጣትነት ዘመን ሁሉንም የመሞከር ፍላጎትና ጥረት የሚስተዋልበት መሆኑን ጠቅሰው በተሻለ አስተሳሰብ ታንጾ ራስን፣ ቤተሰብንና አገርን በሚጠቅም ጉዳይ ላይ ጎልቶ ከታየ አዎንታዊ ምላሽ ይኖረዋል ብለዋል።

"አፍሪካ የቴክኖሎጂ ወይንም የፋይናንስ ሃብታም ሳትሆን የሰው በተለይም የወጣቶች ሃብታም ነች" ያሉት ሚኒስትሯ ወጣቶች አስተሳሰባቸውንና እውቀታቸውን በማዳበር አገራቸውን ኃያላን አገራት የደረሱበት ደረጃ ማድረስ ይችላሉ ብለዋል።

በዋናነት ያላቸውን እምቅ አቅም በሳይንሳዊ መንገድ በመተግበር ለአካባቢያቸውና ለቀጠናቸው ሰላምና ደህንነት ዘብ ሊቆሙ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

በተለይም የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ያለው ተሸፍኖ የሌለው ነገር ጎልቶ የሚታይበት በመሆኑ ይህንን አስተሳሰብ በመቀየር ረገድ የቀጠናው ወጣቶች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።

የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ጌታቸው ሽፈራው፤ ኃይሉ ለአካባቢ ሰላምና ደህንነት እንዲሰራ ታልሞ የተቋቋመ መሆኑን አብራርተዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው ይህ የወጣቶች ሥልጠናም የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ተልዕኮን መሠረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።

ሥልጠናው በኢትዮጵያ እንዲጀመር የተወሰነበት ምክንያትም በአገሪቱ ወቅቱ የአረንጓዴ አሻራ መረሃ-ግብር የሚካሄድበትና ንቅናቄው ለሌሎች አገራት ተምሳሌት በመሆኑ ልምድ እንዲወስዱ ለማስቻል ነው ብለዋል።

ሰላምን የሚሰብኩና በሰላም ዙሪያ መፍትሔን የሚያመጡ የአባል አገራት ልምዶችን የሚለዋወጡበት እድል ይፈጥራል ብለዋል።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው ሥልጠናው በነገው እለትም በእንጦጦ ፓርክ የአረንጓዴ አሻራቸውን የሚያኖሩ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም