ቀጥታ፡

በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ የኢንቨስትመንት ማነቆዎች አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል-አቶ ደመቀ መኮንን

ሰኔ 29 /2013 (ኢዜአ) በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ የኢንቨስትመንት ማነቆዎች አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የውጭ ኢንቨስተሮች የሚያጋጥማቸውን ማነቆዎች ለመፍታት የተቋቋመው ሀገራዊ የቅንጅት መድረክ መደበኛ ስብሰባ ተካሂዷል።

መድረኩን የመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ የኢንቨስትመንት ችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአጠቃላይ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የተጠያቂነት ስርዓትን እስከታች ድረስ በማውረድ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የውጭ ቀጥተኛና ሌሎችም ኢንቨስትመንቶች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ጥቅል ጉዳቱ በሀገር ላይ ነው ያሉት አቶ ደመቀ የሚመለከተው አካል ይህንን ተገንዝቦ ችግሩን የሚመጥን አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ አስገንዝበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጽዮን ተክሉ በሀገሪቱ መዋለ ነዋያቸውን ያፈሰሱ ባለሃብቶች ስለሀገሪቱ ምን ይላሉ በሚል ርዕስ ላይ ገለፃ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሺነር ለሊሴ ነሚ በበኩላቸው የድህረ ኢንቨስትመንት ክትትል ስትራቴጂ አፈጻጸም ያለበትን ደረጃ የገመገመ ጽሁፍ አቅርበው በተነሱት ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዋ ፅዮን በመግለጫቸው ያለፈው ምርጫና በትግራይ ክልል የነበረው ህግ የማስከበር ዘመቻ፤ የብዙ ኢንቨስተሮች ስጋት ነበር ያሉ ሲሆን ፤ሆኖም ግን የጉዳዩን ኣሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ከሰላም ሚኒስቴር፤ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ውጤታማ ተግባር ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

አያያዘውም ኢንቨስትመንትን የማያበረታቱ የተለያዩ ተቋማዊ ችግሮች አሁንም የዘርፉ እድገት ማነቆ በመሆናቸው አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ ከክልሎች ጋር ያለው የቅንጅታዊ አሰራር ክፍተት ዘርፉን እየጎዳው ያለ ተግባር መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሺነር ወይዘሪት ለሊሴ አንስተዋል።

ከፀጥታና መሬት አቅርቦት ጋር ያሉ ችግሮችም የዘርፉ ትልቁ ማነቆ መሆናቸውን ኮሚሽነሯ አንስተዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በዘርፉ ከዚህ ቀደም እንዲሻሻሉ ቅሬታ ከቀረበባቸው መስኮች በኃይል አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መሻሻል መኖሩንም ተናግረዋል።

ከኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ 36 ቅሬታዎች ቀርበው እንደነበር ያስታወሱት ኮሚሽነሯ፤ በአሁን ጊዜ 31 ቅሬታዎች ሙሉ ለሙሉ መፍትሄ ሲያገኙ ሌሎች ቀሪዎቹን ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑን ኮሚሽነሯ አስረድተዋል፡፡

በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ በበኩላቸው በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ የሚታየው የማስፈፀም ችግሮች ዘርፉን እየጎዳው መሆኑን ተናግረዋል።

በሁሉም አካባቢዎች ያሉ የአስፈፃሚና ባለድርሻ አካላት የዘርፉን ጥቅም በሚገባ በመረዳት ማነቆዎችን ፈተው አፋጣኝ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ የውጭ ባለሀብቶች በሚያደርጓቸው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ያጋጥሟቸውን ማነቆዎች የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች አሰራሩ በሚፈቅደው ልክ መፈታት እንዳለበት ጠቁመዋል።

በዚህም ኢትዮጵያን ለባለሃብቱ ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ፣ በችግሮች ዙሪያ የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ አስፈጻሚዎች የጋራ መድረክ በማዘጋጀት እና ባለሀብቱ ከመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመደበኛነት ተገናኝቶ የሚወያይበትን መድረክ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን አቅጣጫ ተቀምጧል።

በመድረኩም ከተለያዩ የፌዴራል፤ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም