በምስራቅ ወለጋ ዞን እና በጎንደር ከተማ ከ540 ሺህ በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሳተፋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ወለጋ ዞን እና በጎንደር ከተማ ከ540 ሺህ በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሳተፋሉ
ነቀምቴ/ ጎንደር ሰኔ 29/2013 (ኢዜአ) በምስራቅ ወለጋ ዞን 440 ሺህ ወጣቶችና ሴቶች የሚሳተፉበት የዜግነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲጀመር በጎንደር ከተማም ከ100 ሺህ በላይ ወጣቶችን በአገልግሎቱ ለማሳተፍ ዝግጀት ተጠናቋል።
የምስራቅ ወለጋ ዞን የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሪት እመቤት በየነ የክረምቱን የዜግነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትናንት በዲጋ ወረዳ ኢፋ ከተማ አስጀምረዋል።
ሀላፊዋ በወቅቱ እንዳሉት በዞኑ ባሉ 17 ወረዳዎች 440ሺህ የሚሆኑ ወጣቶችና ሴቶች በአገልግሎቱ ይሳተፋሉ።
የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች በተገኙበት ትናንት በተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞችን ቤት የመገንባትና የችግኝ ተከላ ሥራዎች ተከናውነዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዓለማየሁ ተስፋ በበኩላቸው በዞኑ በሚገኙ 17 ወረዳዎች ችግኝ የመትከል፣ የአቅመ ደካሞችን ቤትና ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን የመገንባት ሥራዎች እንደሚከናወኑ አመልክተዋል።
የከተሞች ጽዳት በየሳምንቱ በመደበኛው መርሃ ግበር እንደሚከናወን ጠቁመው፤ በዘንድሮ ክረምት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችም እንደሚገነቡ ተናግረዋል።
የተከሏቸውን ችግኞች በመንከባከብ ለፍሬ ለማብቃት እንደሚሰሩ የተናገሩት ደግሞ በችግኝ ተከላው ላይ የተገኙት ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
ወጣት ግዛቸው ብርሃኑ በሰጠው አስተያየት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ በፈጣሪና በሰው ዘንድ መልካም መሆኑን ገልጾ የጀመረውን የበጎ አገልግሎት ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክቷል።
ችግኝ መትከል ግብ እንዳልሆነ የገለጹት ደግሞ የዲጋ ወረዳ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ረጋቱ በቀለ ናቸው።
የተተከሉ ችግኞችን ተመላልሰው በመንከባከብ ለተፈለገው ዓላማ ለማብቃት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በጎንደር ከተማ ከ100 ሺህ በላይ ወጣቶችን ያሳተፈ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማከናወን ዝግጅት መጠናቀቁን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ ለኢዜአ እንዳሉት በከተማው የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሐምሌ 2 ቀን 2013 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች ይጀመራል፡፡
"በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በየክፍለ ከተሞች ከመመልመል ጀምሮ መርሃ ግብሩን ስኬታማ ለማድረግ ወጣቶቹ በሙያቸውና በጾታቸው እንዲደራጁ ተደርጓል" ብለዋል፡፡
መርሃ ግበሩ ሲጀመር ከ20 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች በከተማው ዳርቻ በተዘጋጁ መናፈሻዎችና ፓርኮች እንደሚተከሉ ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡
''በየአመቱ የሚካሄደው የክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የወጣቱን የሥራ ባህል ያጎለብታል'' ያለው ደግሞ የዞብል ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት መንግስቴ ቻላቸው ነው፡፡
የፋሲል ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ቢኒያም ግርማ በበኩሉ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ በመሆን የከተማውን ህዝብ ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡
በጎንደር ከተማ በአረንጓዴ አሻራና በመደበኛ መርሃ ግብር በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ200 ሺህ በላይ ችግኞችን በክረምቱ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በምስራቅ ወለጋ ዞን እንዲሁም በጎንደር ከተማ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ትኩረት ከሚያደርግባቸው መርሃ ግብሮች መካከል የችግኝ ተከላ፣ የአቅም ደካማ መኖሪያ ቤት እድሳትና ግንባታ ይገኙበታል፡፡
የክርምት የማጠናከሪያ ትምህርት፣ በጤናው ዘርፍ የግንዛቤ ማስጨበጫና የደም ልገሳ፣ ወላጅ አልባ ሕፃናትን መርዳት፣ የትራፊክ ደህንነት፣ የከተማ ጽዳትና ውበት፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቦንድ ግዥ ተግባራትም በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ መካተታቸው ታውቋል።