ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን ብዛት ለማወቅ ቆጠራ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ ሀምሌ 30/2010 በአዲስ አበባ የሚገኙ የኢንዱስትሪዎችን ብዛት ለማወቅ የሚያስችል ቆጠራ ሊካሄድ መሆኑ ተገለፀ። የከተማዋ አስተዳደር ዛሬ እንዳስታወቀው በመዲናዋ ምን ያህል ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃ የለም። ይሕም ኢንዱስትሪው ያለበትን ሁኔታ ለማወቅና ዘርፉ የሚፈልገው ድጋፍ ታውቆ እገዛ ለማድረግ እንደሚያስቸግር ነው የተገለፀው። በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጄንሲ ጋር በመሆን ቆጠራውን ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ነው የተጠቆመው። በመዲናዋ የኢንዱስትሪ ቢሮ የጥናት፣ ፕሮሞሽን የኢንዱስትሪ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ኃይለማርያም አብዲሳ እንደገለፁት በከተማው ያሉ ኢንዱስትሪዎች በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃ የለም። ይሄን ክፍተት በጥናት ለመመለስም 21 ሚሊዮን ብር በሚሆን ወጪ ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጄንሲ ጋር በመሆን የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉንና የባለ ኮከብ ሆቴሎች ላይ ቆጠራ ለማካሄድ ስምምነት ተደርጓል። ለዚሁ ተግባርም 580 የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂዎች በጊዚያዊነት የተቀጠሩ ሲሆን ከነገ ጀምሮ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ስልጠና  እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል። የቆጠራ ጥናቱን የሚያግዙ ደግሞ 500 ደምብ አስከባሪዎችም በከተማው አስተዳደር መዘጋጀታቸውንም አመልክተዋል። በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጄንሲ የቢዝነስ ስታቲስቲክስ ዳይሬክተር አቶ ዘለአለም ኃይለጊዮርጊስ በበኩላቸው ቆጠራዉ መካሔዱ ፖሊሲ አርቃቂ አካላትን በግብዓትነት እንደሚጠቅም አንስተዋል። ቆጠራው የኢንዱስትሪዎችን ብዛትና ያሉበት ደረጃ ለማወቅ፣ በዘርፉ ያለው ተሳትፎ በፆታ እና በዕድሜ መለየትን ጨምሮ ምን ያህል የሰለጠነ የሰው ኃይል በስራ ላይ እንዳለ ለማወቅ እንደሚረዳም በመጠቆም። በተጨማም በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በቀላሉ በመለየት ድጋፎችን ለማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል። ቆጠራው ስልጠናው እንደተጠናቀቀ የሚጀመር ሲሆን ለአንድ ወር እንደሚቆይም ነው ያብራሩት። ለዚሁ ቆጠራም የኢንዱስትሪዎች ባለቤቶችና አመራሮች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉም ዳይሬክተሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። ቆጠራው በአዲስ አበባ የሚገኙ ሁሉም በሥራና በዝግጅት ላይ ያሉ ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና አነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን እና ባለኮከብ ሆቴሎችን እንደሚያካትትም ጠቁመዋል። ኤጄንሲው የኢንዱስትሪዎችን ቆጠራ ሲያካሄድ ይሄ የመጀመሪያው መሆኑንም ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም