የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትና ሰራተኞች ከ1 ሺህ በላይ ችግኞችን ተከሉ

60

አዲስ አበባ፣ሰኔ 29/2013 (ኢዜአ) አዲስ አበባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትና ሰራተኞች በአንድ ቀን ከ1 ሺህ በላይ ችግኞችን ተከሉ፡፡

ችግኙን የተከሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ባለፉት ሁለት አመታት ተደምረን የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻውን እንዳሳካነው ሁሉ በዚህ አመትም እጅ ለእጅ ተያይዘን ስራውን እናሳካ ሲሉ "ኢትዮጵያን እናልብሳት "መርኃ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት ጥሪ መሰረት ነው፡፡

በዚህም መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትና ሰራተኞች  የአረንጓዴ አሻራቸውን የካ አካባቢ በመገኘት አሳርፈዋል።

የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ የምክር ቤቱ አባላትና ሰራተኞች በዛሬው እለት ከ1 ሺህ በላይ ችግኞችን በመትከል በመርኃ ግብሩ መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡

የምክር ቤቱ ሰራተኞች ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ለውጤት እንዲበቁ በፕሮግራም እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡

ቀደም ብለው በምክር ቤቱ ከተተከሉ ችግኞች 85 በመቶ መጽደቃቸውንም ምክትል አፈ ጉባዔዋ አስታውቀዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባል የሆኑት አቶ ሽብሩ እሸቱ፤ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ችግኝ መትከል ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የአፈር መሽርሸርን ለመግታት፣ ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ ለማግኘትና የህዳሴ ግድብ ተፋሰስ ወንዞችን ህልውና ለመጠበቅ በየጊዜው ችግኝ መትክል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የአገሪቱን የቀደመ የአረንጓዴ ገፅታ ለመመለስ ሁሉም ህብረተሰብ ችግኞችን በመትከል እንዲሳተፍ አስገንዝበዋል ፡፡

ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመጣው የመሬት መራቆት ሳቢያ ብቻ  በየዓመቱ እስከ 40 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደምታጣ ይገመታል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት የተሰራው የአረንጓዴ አሻራ ስራ ይህን ችግር ለማቃለል እየተሰራ ይገኛል።

በዚህ ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ 6 ቢሊየን ችግኝ የሚተከል ሲሆን ለጎረቤት ሀገራት ደግሞ 1 ቢሊየን ችግኞች መዛጀታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም