የኢትዮጵያ መርከብ በበርበራ ወደብ አገልግሎት መስጠት ጀመረች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መርከብ በበርበራ ወደብ አገልግሎት መስጠት ጀመረች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መርከብ ከ20 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶማሌ ላንድ በርበራ ወደብ መደበኛ የጭነት አገልግሎት መስጠት ጀመረች።
"ጊቤ" የሚል ስያሜ ያላት መርከብ "ገልፍ ኢንዲያ ሰብ ኮንቲነንት" ከሚባለው አካባቢ 11 ሺህ 200 ቶን ስኳርና ሩዝ በመጫን ትናንት በርበራ ወደብ ደርሳለች።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት መርከብ የሆነችው "ጊቤ" ወደ ስፍራው ስትገባ አቀባበል ተደርጎላታል።
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ፣ በሶማሊያ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል ሰኢድ መሐመድ ጅብሪል እና ሌሎች የሚመለከታቸው የዱባይ ፖርትስ ወርልድ (ዲፒ ወርልድ) የወደብ አስተዳደር ሃላፊዎች በወደቡ ተገኝተው አቀባበል አድርገዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ መርከብ በበርበራ ወደብ ከ20 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መደበኛ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ድርጅቱ ገልጿል።
መርከቧ በአሁኑ ጉዞዋ 11 ሺህ 200 ቶን ስኳርና ሩዝ ይዛ ለሶማሌ ላንድ ገበያ ማጓጓዟ የተነገረ ሲሆን ሸበሌ የተሰኘችው ሌላኛዋ የኢትዮጵያ መርከብ "ገልፍ ኢንዲያ ሰብ ኮንቲነንት" ከሚባለው አካባቢ ተመሳሳይ መጠን ያለው ጭነት ይዛ ከሳምንት በኋላ በርበራ ወደብ እንደምትደርስ ተነግሯል።
ጊቤና ሸበሌ መርከቦች በ"ገልፍ ኢንዲያ ሰብ ኮንቲነንት" ባለው መስመር እቃን የማጓጓዝ ስራ እንደሚያከናውኑ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መርከቦች በበርበራ ወደብ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው በወደቡ ያለውን አገልግሎት በማጠናከር የድርጅቱን የአገልግሎት ሽፋን ለማስፋትና ለማሳደግ የያዘው እቅድ አካል ነው ተብሏል።
የበርበራ-ኢትዮጵያ ኮሪደር ለኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ ተወዳዳሪ አገልግሎት ለመስጠት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታምኖበታል።
በበርበራ ወደብ ላይ የተሰማሩ በርካታ ባለሃብቶችና አገራት የማልማትና የመገልገል ጥያቄ እያቀረቡና የስራ ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውን የገለጸው ድርጅቱ የወደቡ ዓለማቀፋዊ ተቀባይነትና አመቺነት ለገቢና ወጪ ንግድ ገቢው የራሱ አበርክቶ ይኖረዋል ብሏል።
ጊቤና ሸበሌ መርከቦች በተመሳሳይ 28 ቶን ጭነት የመያዝ አቅም ያላቸው ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ኖታ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ዘጠኝ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡና ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች አላት፤ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡት መርከቦች በተመሳሳይ 28 ሺህ ቶን የመጫን አቅም ያላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሁለቱ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች እያንዳንዳቸው 40 ሺህ ሜትሪክ ቶን ነዳጅ የማንሳት አቅም እንዳላቸው ነው አቶ አሸብር ያስረዱት።
በበርበራ ወደብ ያለው የገበያ አቅም በማየት ተጨማሪ መርከቦችን ወደ ስራ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በራሷ መርከብና ከዓለም አቀፍ የመርከብ ድርጅቶች ጋር ውል በመፈራረም የእነሱን መርከቦች ተጠቅማ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የወጪና የገቢ ንግዷን የምታከናውነው በጅቡቲ ወደብ መሆኑን አቶ አሸብር አስታውሰዋል።