የሎጂስቲክ ዘርፍ አፈጻጸም መታወቅ ዘርፉን ለማዘመንና ለውጥ ለማምጣት ያስችላል - ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ - ኢዜአ አማርኛ
የሎጂስቲክ ዘርፍ አፈጻጸም መታወቅ ዘርፉን ለማዘመንና ለውጥ ለማምጣት ያስችላል - ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ
ሰኔ 29 ቀን 2013 (ኢዜአ) የሎጂስቲክ ዘርፍ አፈጻጸም መታወቅ ዘርፉን ለማዘመንና እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችል የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ።
የመጀመሪያው አገራዊ የሎጂስቲክ አፈጻጸም ሪፖርት ይፋ በተደረገበት መርሐግብር ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ወይዘሮ ዳግማዊት “የሎጂስቲክ ዘርፍ አፈጻጻም ደረጃ የወጪ ንግድ ስርዓቱን ለመገምገም የሚያስችል ነው” ብለዋል።
“የዘርፉ አፈጻጸም መታወቅ የአገራትን ሳቢነት የሚያሳይና የኢንቨስትመንት እድልን የሚፈጥር ነው” ያሉት ሚኒስትሯ፤ የአለም ባንክ በየአመቱ የሎጂስቲክ አፈጻጸምን በመገምገም የአገራትን ደረጃ እንደሚያስቀምጥ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያም በ10 አመቱ የትራንስፖርት መሪ ዕቅድ ላይ ሎጂስቲክ ዘርፉን ዋና አካል በማድረግ እየሰራች እንደምትገኝም ጠቅሰዋል።
አለምአቀፋዊ መመዘኛዎችን ያካተተ በአገር በቀል ዕውቀት የተዘጋጀ የሎጂስቲክ አፈጻጸም ለዘርፉ ስኬት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
“አፈጻጸምሙ መታወቁ ዘርፉን ለማዘመንና እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል” ብለዋል። አክለውም የአፈጻጸሙ መታወቅ በሣይንሳዊ መንገድ ለመመራት፣ ወደ ዲጂታል አገልግሎት ለማደግ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታን ለማሳለጥና የመረጃ እጥረትን ለመቀነስ እንደሚያስችልም አብራርተዋል።