ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዚህ ሳምንት የተጠቃለለ የምርጫ ውጤት ይፋ እንደሚያደርግ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዚህ ሳምንት የተጠቃለለ የምርጫ ውጤት ይፋ እንደሚያደርግ ገለጸ
ሰኔ 28/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዚህ ሳምንት የተጠቃለለ የምርጫ ውጤት ይፋ እንደሚያደርግ ገለጸ ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ሶሊያና ሽመልስ በሰጡት መግለጫ ድምጽ በተሰጠባቸው ሁሉም የምርጫ ክልሎች ውጤት ተጠቃሎ ገብቷል።
ባለፈው ሳምንት ለቦርዱ ያልደረሱ 30 የምርጫ ውጤቶች አሁን ተጠቃለው ገብተዋል ብለዋል።
በመሆኑም በዚህ ሳምንት የተጠቃለለ የምርጫ ውጤት ቦርዱ እንደሚያሳውቅ ኃላፊዋ ገልጸዋል።
በደቡብ ክልል ተቋርጦ የነበረው የቁጫ ምርጫ ክልል የድምጽ ቆጠራ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ሰባቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች ባሉበት ቆጠራ ተጀምሯል ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል ነገሌ ምርጫ ክልል አንድ የግል ተወዳዳሪ "በምርጫ ወረቀቱ ላይ ስሜ አልተካተተም" በሚል ያቀረቡት ቅሬታ ተቀባይነት በማግኘቱ ቦርዱ ቅሬታው አሳማኝ መሆኑን አረጋግጦ ምርጫ እንዳይካሄድ ወስኖ እንደነበር ይታወቃል።
ሆኖም ቅሬታ አቅራቢው የግል ተወዳዳሪ ምርጫ ከተደረገ በኋላ "በእኔ ምክንያት ድጋሜ ምርጫ መካሄድ የለበትም" በማለቱ ውጤቱ እንዲቆጠር ቦርዱ ወስኖ ነበር።
በውሳኔው መሰረትም በነገሌ የምርጫ ክልል ድምፅ ያልተሰጠባቸው 30 የምርጫ ጣቢያዎች በቀጣይ ሐሙስ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ድምጽ ይሰጣል ብለዋል ኃላፊዋ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ 31 የፓለቲካ ፓርቲዎችና የግል እጩ ተወዳዳሪዎች ደቡብ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሲዳማ፣ አማራ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደሮች ከ160 በላይ አቤቱታዎችን አቅርበዋል ብለዋል።
ቦርዱ ባቋቋመው የሕግ ቡድን አማካኝነት አቤቱታዎቹን መርምሮ በሚደርስበት ውጤት በቀጣይ ቀናት ለፖለቲካ ፓርቲዎችና ለሚመለከታቸው አካላት ውሳኔውን ያሳውቃል ብለዋል።