ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላቀረቡት አቤቱታ በሚመለከት በዚህ ሳምንት ምላሽ እንደሚሰጥ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላቀረቡት አቤቱታ በሚመለከት በዚህ ሳምንት ምላሽ እንደሚሰጥ አስታወቀ
ሰኔ 28/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላቀረቡት አቤቱታ በዚህ ሳምንት ምላሽ እንደሚሰጥ አስታወቀ።
የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል እጩ ተወዳዳሪዎች 165 የሚጠጉ የምርጫ ክልሎች ላይ አቤቱታ ማቅረባቸውን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮምዩኒኬሽን ሃላፊ ሶሊያና ሽመልስ በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረቡ አቤቱታዎች እያስተናገደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ቦርድ የሕግ ባለሙያዎችን በመመደብ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል እጩ ተወዳዳሪዎች ላቀረቡት አቤቱታ የሕግ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
እስካሁን 31 የፓለቲካ ፓርቲዎችና የግል እጩ ተወዳዳሪዎች በ165 የምርጫ ክልሎች ላይ አቤቱታ ማቅረባቸውን አስታውሰው አቤቱዎቹ የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶችን የሚያጠቃልል ነው ብለዋል።
ደቡብ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሲዳማ፣ አማራ፣ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳሮች አቤቱታ ከቀረበባቸው የምርጫ ክልሎች ይጠቀሳሉ።
በአማራ ክልል በ49 የምርጫ ክልሎች፣ በደቡብ ክልል 40 የምርጫ ክልሎች፣ በአዲስ አበባ 23ቱም የምርጫ ክልሎችና አፋር 21 የምርጫ ክልል ላይ አቤቱታ መቅረባቸውን ሶሊያና ገልጸዋል።
ሲዳማ ክልል ስምንት የምርጫ ክልሎች፣ የኦሮሚያ ክልል ሁለት የምርጫ ክልሎችና ድሬዳዋ አንድ የምርጫ ክልል አቤቱታ መቅረቡንም አመልክተዋል።
አቤቱታዎቹ አስተዳደራዊ እርምጃ ይወሰድና ውጤት ተሰርዞ ድጋሚ ምርጫ ይካሄድ በሚሉት ጉዳዮች ውስጥ የሚወድቁ ናቸው፤ ይሁንና በተወሰነ ደረጃ ድጋሚ ቆጠራ ይካሄድ የሚሉ አቤቱታዎች መቅረባቸውንም ነው ያስረዱት።
ቦርዱ በድምጽ አሰጣጡ ቀን የቀረቡትን አቤቱታዎች ሲቀበል መቆየቱን ገልጸው አንዳንዶቹ አቤቱታዎች በምርጫ ጣቢያ ምላሽ እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸው አቤቱታዎች ቦርዱ ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች እንዲያሟሉ የማድረግ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው በአሁኑ ሰዓት የቀረቡ አቤቱታዎች የመመርመር ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቋቋመው የሕግ ቡድን አማካኝነት አቤቱታዎቹን እየመረመረ እንደሚገኝና ቡድኑ የሚያቀርባቸውን ውሳኔዎች መሰረት በማድረግ ቦርዱ እስከ ሐሙስ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ለፖለቲካ ፓርቲዎችና ለሚመለከታቸው አካላት ውሳኔውን ያሳውቃል ብለዋል።
በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ከ37 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በጸጥታ ችግር፣ የድምጽ መስጫ ወረቀት ሕትመት ችግር ባለባቸውና የፍርድ ቤት ውሳኔ በተሰጠባቸው የምርጫ ክልሎች ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም ድምጽ እንዲሰጥ ቦርዱ ወስኗል።
በተጨማሪም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ በተመሳሳይ ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል።