በበጀት ዓመቱ የሀገር ውስጥ ምርትን በመጨመር የዋጋ ንረትን ማረጋጋት ላይ ትኩረት እንሰጣለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ የሀገር ውስጥ ምርትን በመጨመር የዋጋ ንረትን ማረጋጋት ላይ ትኩረት እንሰጣለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
ሰኔ 28/2013 (ኢዜአ) በ2014 በጀት ዓመት የሀገር ውስጥ ምርትን በመጨመር የዋጋ ንረትን ማረጋጋት ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
መንግስት የወሰደው የተናጥል ተኩስ አቁም ልማትና ገበያ ማረጋጋት ላይ የተሻለ ስራ እንዲከናወን እድል አንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ ነው።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የፌደራል መንግስት የ2014 በጀት 561 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ሆኖ እንዲጸድቅ የቀረበውን ሃሳብ መርምሮ አጽድቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህን ወቅት የ2013 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ካለፈው ዓመት በተሻለ መልኩ እድገት ማስመዝገቡን አመላካቾች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ ከቡና ወጪ ንግድ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገዳማ፤ እንዲሁም ከወርቅ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን አንስተዋል።
በሙከራ ደረጃ በተተገበረው የበጋ ስንዴ ግብርና 15 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱንም ጠቅሰዋል።
በበጀት ዓመቱ ከወጪ ንግድ ብቻ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ጠቁመው፤ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ18 በመቶ እድገት አሳይቷል ነው ያሉት።
የገቢ ንግድ በዜሮ ነጥብ 6 በመቶ ብቻ ማደጉንና ይህም የንግድ ሚዛን ላይ የተሻለ ለውጥ መኖሩን አመላካች እንደሆነ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ጥቅል ሀገራዊ ምርት 4 ነጥብ 2 ትሪሊዮን መድረሱንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
በዚህ ሁሉ የምጣኔ ሃብት ስኬት ውስጥ የዋጋ ግሽበት አሁንም የኢትዮጵያ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን ገልጸው፤ መንግስት ችግሩን ለማቃለል የተለያዩ ስልተችን ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል።
መንግስት የምግብ ሸቀጦችን ከውጭ ከማቅረብ ባሻገር የህብረት ስራ ማህበራት የተሻለ ብድር አግኝተው መሰረታዊ ፍጆታዎችን በዝቅተኛ ዋጋ የእንዲያቀርቡ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በቅርቡም ከመንግስት በጀት ውጭ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የዳቦ ፋብሪካዎች በመገንባት ችግሩን ለማቃለል ይሰራል ብለዋል ።
የዋጋ ግሽበትን ስር ነቀል በሆነ መንገድ መፍታት የሚቻለው "በምርት እድገት" ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አንጻር ምርታማነትን ለመጨመር በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በተያዘው ክረምት "አንድም መሬት ጾም ማደር የለበትም" በሚል እሳቤ የእርሻ ስራ በስፋት እንደሚከናወንም ተናግረዋል።
በሙከራ ደረጃ የተሻለ ምርት የተገኘበትን የበጋ ስንዴ እርሻን አጠናክሮ መቀጠልም እንዲሁ።
በተያያዘ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ያደረገው የተናጥል ተኩስ አቁም ልማትና ገበያ ማረጋጋት ላይ የተሻለ እንዲሰራ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ወስጥ ፈተኙ ስራ በአጭር ጊዜ እድገትና ብልፅግናን መማምጣት እንጂ ጦርነት መፍጠርና ማራዘም አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስት ከዚህ አንጻር ለኢትዮጵያ የሚበጀውን መወሰኑን ገልጸዋል።
"ዶላር እየተኮሱ ልማትንና የተራበ ህዝብን ማሰብ አይቻልም" ሲሉም ተናግረዋል።
የመንግስት ውሳኔ ህዝብ የሚጠብቃቸውን ፕሮጀክቶችና በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን በመደገፍ ረገድ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
መንግስት የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ በጥልቀት በመመርመር የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፉንም ጨምረው ገልጸዋል።