በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድህነትን ለመቀነስ ተጨማሪ የልማት እቅድ ተዘጋጀ

60
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የህዝቡን እውቀትና ሃብት በመጠቀም ድህነትን ለመቀነስ ለተዘጋጀው ተጨማሪ የልማት እቅድ ሁሉም አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ጥሪ አቀረቡ፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ ትናንት የክልሉ ምክር ቤት ሰባተኛ መደበኛ ጉባኤ ሲጠናቀቅ እንዳሉት የክልሉ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በማልማት ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች በመደበኛ ሥራ ብቻ ሊሳካ እንደማይችል የክልሉ መንግስት ተረድቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ድህነትን ለመቀነስ ተጨማሪ የልማት እቅድ ተዘጋጅቶ ከመጪው ጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡ የዚሁ የልማት እቅድ ዓላማ የህብረተሰቡን ሃብትና እውቀት በማስተባበር ተጨማሪ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ድህነትን መቀነስ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በተለይ በግብርና፣ በእንስሳት እርባታ፣ በባህላዊ ወርቅ ማምረት፣ በከተማ ጥቃቅንና አነስተኛ የተሠማሩት አካላት ላይ እንደሚያተኩር ጠቁመዋል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት እነዚህ አካላት በቂ ብድር፣ መሠረታዊ እውቀት፣ ዘመናዊ የግብርናና የማእድን ማምረቻ መሣሪያዎችን በማግኘት ምርታማ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ “ለፕሮጀክቱ የሚያስፈገው በጀት ደግሞ ከአርሶ አደሩ፣ ከመንግስት ሠራተኛው፣ ከባለሃብቶች፣ ከነጋዴዎችና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ይሰበሰባል'' ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱን የሚያስፈጽም ህብረተሰቡን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ የሚቋቋም ሲሆን ሥራውን ራሳቸው እንደሚመሩት ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡ በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ አካላት ድጋፍና እገዛ እንዳይለያቸውም አቶ አሻድሊ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ አልከድር አህመድ ተጨማሪ የልማት እቅዱ በተለይም በሥራ እጦትና በአደንዛዥ እጽ ተገፋፍተው ወደ ጥፋት የሚገቡ ወጣቶችን በሀገር ኢኮኖሚ እንደሚያሳትፍ ገልጸዋል፡፡ ይህም አሁን የሚታየውን የኑሮ ውድነት በመቀነስ ሁሉንም ህብረተሰብ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡ እቅዱን ፈጥኖ ወደ ህብረተሰቡ ማውረድ እንደሚገባ ጠቅሰው በተለይ በመደበኛ የልማት ሥራዎች የተገኙ ተሞክሮዎችን በአግባቡ በመጠቀም ውጤት ማምጣት እንደሚገባ መክረዋል፡፡ አቶ ደስታየሁ ምት በበኩላቸው “ህብረተሰቡን ያሳተፈ ግልጽነት የተሞላው አካሄድ ከተከተልን እቅዱ ይሳካል” ሲሉ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ የምክር ቤቱ አባላት አረጋግጠዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም