ቀጥታ፡

የፋይናንስ ተቋማት ለሰላም ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

ሰኔ 28/ 2013 (ኢዜአ) ሀገር በቀል የፋይናንስ ተቋማት በሰላምና የአብሮነት እሴት ግንባታ ላይ የድርሻቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ተጠየቀ።

በኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስተባባሪነት " የኃይማኖትና አገር በቀል የፋይናንስ ተቋማት በአገር ግንባታ ላይ የሚኖራቸው ሚና" በሚል መሪ ሃገራዊ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዳሉት፤ ጉባኤው በአገሪቷ ሠላምን ለማስፈን፣ በሕዝቦች መካከል መከባበር እንዲኖርና ግጭቶች እንዲቀንሱ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰፊ ተግባር ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

በእርቀ ሰላም ማስፈን ተግባርና በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል ዙሪያም ሰፊ ሥራ ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡

ትውልድ በስነ-ምግባር ታንጾ እንዲያድግም በሁሉም የኃይማኖት ተቋማት የስነ-ምግባር ትምህርቶች በመስጠት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ጉባኤው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰላም ግንባታ ሥራውን ከማገዝ አንጻር ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው የፋይናንስ ተቋማት በሀገር ሰላም፣ መከባበር፣ አብሮነት እሴት ግንባታ፣ ትውልድን በግብረ-ገብ የማነጽ ተግባር ላይ የሚሰሩትን ስራዎችን በመደገፍ የንግድ እንቅስቃሴያቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያካሂዱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጉባኤው የጀመረውን ሰላም የማስፈንና ትውልዱን በስነ-ምግባር የማነጽ ተግባር አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው በበኩላቸው፤ ጉባኤው ለህዝብ ጠቀሜታ ያላቸውን  ሀገራዊ የሰላም ግንባታ ሥራ የሚያከናውነው ስራ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚሀም ሀገር በቀል የፋይናንስ ተቋማት በበጀት በመደገፍ መልካም ጅማሮውን እንዲያስቀጥል ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ፤ ባንኩ ለሰላም ግንባታ የሚሰሩ ተቋማትን ለማገዝ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ መቻቻልን፣ መከባበርን፣ መረዳዳትንና ሠላም ማስፈን ሂደት በተለይ የኃይማኖት ተቋማት ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የምክክር መድረኩ ተሳታፊ የኃይማኖት አባቶች በሰጡት አስተያየትም የኃይማኖት ተቋማት ለሃገር ዕድገትና ልማት አስተዋፇው ብዙ መሆኑን ጠቅሰው ይህን ሥራቸውን በፋይናንስ መደገፍም ተገቢ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የኃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም