ቀጥታ፡

በመተከል እየተካሄ ያለው እርቅ ውጤት እያስመዘገበ ነው - ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ

ሰኔ 28 ቀን 2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን የተፈጠረውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታትና ሰላም ለማስፈን እየተካሄደ ያለው እርቅ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የዞኑ የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ ተናገሩ።

በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ጫካ ገብተው ሲንቀሳቀሱ ለቆዩ ታጣቂዎች የተሰጠው የተሃድሶ ስልጠና ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት ሌተናል ጄኔራል አስራት፤ ኮማንድ ፖስቱ ሰላምን ለመመለስ የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅሟል።

እስካሁን ከ2 ሺ 100 በላይ ታጣቂዎች በሁለት ዙር የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውን ገልጸዋል።

ታጣቂዎቹ ከህብረተሰቡ ጋር እርቅ በማከናወን ይቅር መባባላቸው በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም ተፈጥሮ መልካም ውጤት ሊመዘገብ መቻሉን አብራርተዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ "ከቀደመው ባህላችን፣ እምነታችንና መልካም እሴቶቻችን እርቀን ያልተገባ ችግር ውስጥ ገብተናል" ብለዋል።

በዚህም በርካታ እናቶች፣ አዛውንቶችና ህጻናት ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ገልጸው፤ የጥፋት ድርጊትን ማውገዝና ዳግም እንዳይከሰት መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በዞኑ በደረሰ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ምክንያት አርሶ አደሩን ለጉስቁልና መዳረጉን ተናግረዋል።

የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት የማረጋገጥ አስፈላጊነት ጠቁመው፤ አርሶ አደሩ ወደ የመኖሪያ ቀየው ተመልሶ ማሳውን እንዲያለማ የተጀመሩ ጥረቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥና የኮማንድ ፖስቱ አባል ብርጋዴር ጄኔራል አለማየው ወልዴ የስነ ልቦና ዝግጁነት እና የጉምዝ ህዝብ እሴትና የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የተሃድሶ ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

ህገ መንግስትና ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት፣ አገራዊ ለውጥና የጉምዝ ህዝብ የተጠቃሚነት ጥያቄና የስራ እድል ፈጠራ፣ ወንጀልን መከላከልና ስነ ምግባርና የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች የተሃድሶ ስልጠናው አካል እንደነበሩ ጠቁመዋል።

ኮማንድ ፖስቱ ወደ ስራ ከገባ ወዲህ ባከናወናቸው የሰላም ማስፈን ሂደቶች በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ሰላም ወደ ቀድሞ ሁኔታ እየተመለሰ መሆኑን የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ ገልጸዋል።

ለዚህ ስኬት የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት፣ ለአማራና ኦሮሚያ ክልል መንግስታት አመራር አባላትና አባላት ምስጋና አቅርበዋል።

የመተከል ዞን በብዝሃነት መገለጫነቷ ትንሿ ኢትዮጵያ መሆኗን መረዳት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ "ሁሉም የዞኑ ነዋሪ አብሮነትና ዘላቂ ሰላምን በማጠናከር ከጸጋዋ ተጠቃሚ መሆን ይኖርበታል" ብለዋል።

ኮማንድ ፖስቱ የዞኑን ሰላም ለመመለስ ሲያደርግ በነበረው ጥረት አሰተዋጾኦ ላደረጉ አካላት እውቅና ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም