ቀጥታ፡

ኢዜአ በመተከል ዞን ሰላም ለማምጣት ላበረከተው አስተዋጽኦ የዞኑ ኮማንድ ፖስት አመሰገነ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልገሎት (ኢዜአ) በመተከል ዞን ትክክለኛና በመረጃ የተደገፈ ዜና በመዘገብ ሰላም ለማምጣት ላበረከተው አስተዋጽኦ የዞኑ ኮማንድ ፖስት ምስጋና አቀረበ።

የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት የዞኑን ሰላም ለመመለስ በተደረገው ጥረት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርቧል። 


ኢዜአ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ታሪክ ከ79 ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረ የዜና አገልግሎት ተግባር በማከናወን ላይ የሚገኝ ብቸኛው ተቋም ነው፡፡


ተቋሙ የተለያዩ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌሎች ጉዳዮችን የሚዳስሱ ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ አድርሷል፤ በማድረስም ላይ ይገኛል።


የህዝብና መንግስት የመረጃ ድልድይ በመሆን የህዝብ ተደራሽነቱን በማዕከል፣ ዞንና ወረዳ ጭምር በማስፋት እያገለገለ ይገኛል።


አገራዊ ተልዕኮውን እውን ለማድረግም መንግስትና ህዝብ በሚፈልጉበት ቦታ ሁሉ በመግባት መረጃን እያቀረበ ነው።


በቅርቡም በመተከል ዞን ተከስቶ የነበረውን ግጭት ወደ ነበረበት ለመመለስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ላለፉት ስድስት ወራት በስራ ላይ በነበረበት ወቅት ኢዜአ በብቸኝነት መረጃ በማድረስ የድርሻውን ተወጥቷል።


ለዚህም ኮማንድ ፖስቱ ለኢዜአ የላቀ ምስጋና አቅርቧል።

የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት ዋና ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ፤ ኢዜአ የዞኑን ሰላም ለመመለስ በተደረገው ጥረት የላቀ ሚና እንደነበረው ገልጸዋል።

ኢዜአ በዞኑ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ በመረጃ አስደግፎ በመዘገብና ለህዝቡ የተጣራና ትክክለኛ መረጃ የተሳካ ስራ አከናውኗል ብለዋል።

ለዚህም ምስጋና እና አክብሮት ይገባዋል ብለዋል ሌተናል ጄኔራል አስራት።ትክክለኛ 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በ1934 ዓ.ም የተመሰረተ ብቸኛው የአገሪቷ የዜና አገልግሎት ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም