ቀጥታ፡

የኤ.አይ.ቪ/ ኤድስ ህሙማንን የሽንት ናሙና በመጠቀም የቲቢ በሽታ መመርመር የሚያስችል ዘዴ ይፋ ሆነ

ሰኔ 28/2013 (ኢዜአ) የኤ.አይ.ቪ/ ኤድስ ህሙማንን የሽንት ናሙና በመጠቀም የቲቢ በሽታን መመርመር የሚያስችል የምርመራ ዘዴ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጽጌረዳ ክፍሌ፣ የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል።

በዕለቱ ኢንስትቲዩቱ ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ህሙማን ላይ የሽንት ናሙናን በመጠቀም የቲቢ በሽታን መመርመር የሚያስችል የምርመራ ዘዴ ይፋ አድርጓል።

የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ህሙማን በሸታው በሚፈጥረው የሰውነት የመከላከል አቅም ማነስ ምክንያት የተለመደውን የቲቢ አክታ ናሙና ለመስጠት እንደሚቸግራቸው ዶክተር ጽጌረዳ ጠቁመው፤ ናሙናው የቲቢን በሽታ የማመላከት ችግር እንደነበረው ገልጸዋል።

ከሕመምተኞቹ የሚወሰደው ናሙና ጥራቱን የጠበቀ ያለመሆኑን ዶክተር ጽጌረዳ ጠቁመው፤ ብዙ ጊዜ የቲቢ በሽታን በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ህሙማንን ለመመርመር አዳጋች እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያትም የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ህሙማን የቲቢ ምርመራ ሳያካሂዱ ለሞት እንደሚዳረጉም ገልጸዋል።

ዶክተር ጽጌረዳ፤ ከመደበኛው የቲቢ መመርመሪያዎችና ናሙናዎች ውጭ ለኤች.አይ.ቪ ህሙማን የሚሆን የቲቢ ምርመራ ዘዴዎች በተጓዳኝ ማቅረብ ማስፈለጉን ጠቁመው፤ የሽንት ናሙናን በመጠቀም የቲቢ መመርመሪያ ዘዴ ይፋ ማድረግ እንዳስፈለገ አብራርተዋል።

ምርመራው የኤች.አይ.ቪ ህመም ለጠናባቸው እና የሲዲ ፎር መጠናቸው ዝቅ ላሉ ህሙማን ቲቢን የመመርመር አቅም ከፍ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት።

ምርመራው በዓለም ጤና ድርጅት ምክረ - ሐሳብ መሰረት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት እና የጤና ሚኒስቴር ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ምርመራው በኤች.አይ.ቪ ህክምና መከታተያ ተቋማት እንደሚተገበር ነው ዶክተር ጽጌረዳ የተናገሩት።

በዓለም ላይ በዓመት 10 ሚሊዮን የሚጠጉ አዲስ የቲቢ በሽተኞች ሪፖርት እንደሚደረግ ገልፀው፤ ከእነዚህ መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ የዓለም ጤና ድርጅትን በመጥቀስ ዶክተር ጽጌረዳ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም