በህግ ማስከበር ዘመቻው መከላከያ አገራዊ ቁመና ይዞ ጠንካራ ሆኖ እንዲገነባ የሚያስችል ዕድልና ልምድ ተገኝቷል - ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
በህግ ማስከበር ዘመቻው መከላከያ አገራዊ ቁመና ይዞ ጠንካራ ሆኖ እንዲገነባ የሚያስችል ዕድልና ልምድ ተገኝቷል - ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ
ሰኔ 28 ቀን 2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ከምንም በላይ መከላከያ አገራዊ ቁመና ይዞ ጠንካራ ሆኖ እንዲገነባ የሚያስችል ዕድልና ልምድ ተገኝቷል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ እየሰጡ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በህግ ማስከበር ዘመቻው የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
በገለጻቸው ወደ ህግ ማስከበር ዘመቻ ለመግባት አስገዳጅ የሆነው ችግር ግንባር ቀደም ምንጭ የሆኑ አካላት ላይ ከርምጃ እንደተወሰደባቸውና ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉንም ተናግረዋል።
ቀሪዎቹ ደግሞ ዳግም የተመሳሳይ ጥፋት እንዳያስከትሉ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
“ሰሜን ዕዝ ነጻ ወጥቷል፣ ትጥቃችን ተመልሷል፣ ጎንደር፣ ባህርዳርና አስመራ የሚተኮስበት ሚሳኤል ተመልሷል፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በብድር የገዛው ሚሳኤል መልሶ ኢትዮጵያን ከማጥፋት እንዲቆም ተደርጓል” ብለዋል።
“ሰሜን ዕዝን ቀምተን ትጥቃችንን አዳብረን እንደፈለግን እናደርጋለን የሚለው ሃሳብ የማይሳካ መሆኑን ለማሳየት ተሞክሯል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከሁሉ በላይ መከላከያ አገራዊ ቁመና ይዞ ጠንካራ ሆኖ እንዲገነባ በምንም መንገድ የማይገኝ መልካም ዕድልና ልምድ መገኘቱን አብራርተዋል። ከዚያ በፊት በነበረው ሁኔታ የሚታቀዱ ዕቅዶች ላይ የጥፋት ሃይሉ እኩል ይሰማ ስለነበረ ምንም ነገር መስራት እንደማይቻል አስታውሰዋል።