ቀጥታ፡

የሃይማኖትና አገር በቀል የፋይናንስ ተቋማት በአገር ግንባታ ላይ በሚኖራቸው ሚና ላይ ምክክር እየተካሔደ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሰኔ 28/2013 የሃይማኖትና አገር በቀል የፋይናንስ ተቋማት በአገር ግንባታ ላይ በሚኖራቸው ሚና ላይ ምክክር እየተካሔደ ነው።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመተባበር ያዘጋጁት የምክክር መድረክ "የሃይማኖትና አገር በቀል የፋይናንስ ተቋማት በአገር ግንባታ ላይ የሚኖራቸው ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ ነው። 

ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት የተውጣጡ አባቶችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።


የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ በአገሪቷ ሠላምን ለማምጣት፣ በሕዝቦች መካከል መከባበር እንዲኖርና ግጭቶች እንዲቀንሱ ከማድረግ አንፃር በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ጉባኤው ይሕንኑ የሠላምና የማህበረሰብ ግንባታውን በተጠናከረ መንገድ እንዲያስኬድ ለማስቻል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጉልሕ ሚና መጫወቱን ጠቅሰዋል።


የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሣኖ በበኩላቸው ባንኩ ሠላምን ለሰላም ግንባታ የሚሰሩ ተቋማትን ለማገዝ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።


በኢትዮጵያ መቻቻልን፣ መከባበርን፣ መረዳዳትንና ሠላም የማስፈን ስራቸውን የሃይማኖት ተቋማት አጠናክረው እንዲቀጥሉ የማድረግም ያስፈልጋል ብለዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው፤ የፋይናንስ ተቋማት በአገሪቱ በሠላም ግንባታ ዙሪያ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራታቸውን መልካም ጅምር ብለውታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም