ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ጠቅላላ የብድር ጫና እየተቃለለ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

 አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሰኔ 28/2013 የኢትዮጵያ ጠቅላላ የብድር ጫና ከአገራዊ ጠቅላላ ምርት አንጻር 26 በመቶ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ ልዩ ስብሰባውን እያካሄደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በምክር ቤቱ ሰብሰባ ላይ በመገኘት ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄና አስተያየቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስተሩ በማብራሪያቸው የብድር ጫናው ከጠቅላላ አገራዊ ምርት ጋር ሲነጻጸር ከዚህ ቀደም 37 በመቶ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ 26 በመቶ ደርሷል ብለዋል።

ይህም ከአጠቃላይ እዳው አንጻር ሲታይ ብቻ መሆኑን ገልጸው ነገር ግን እዳው ከሚከፈልበት ጊዜ ሲሰላ በብዙ መጠን ቅናሽ ማሳየቱን አብራርተዋል።

ለዚህም ደግሞ በዋነኝነት ባለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ የኮሜርሻል ብድር ሙሉ በሙሉ ማቆሟን ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት የኮሜርሻል ብድር የአገሪቱን የብድር ጫና ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርስ ትልቅ አስተዋጽዖ ማድረጉንም አንስተዋል።

በሌላ በኩል አገሪቱ ያለባትን የብድር ጫና ለማስተካከል ከወዳጅ አገራት ጋር የተሰሩ ሥራዎች ለተገኘው ውጤት በምክንያትነት አስቀምጠዋል።

በተጓዳኝም አገሪቱ ያለባትን አንዳንድ ብድሮች  መክፈል መቻሏን ጠቅሰው በድምሩ የብድር ጫናው በእጅጉ እንዲቃለል መቻሉን ነው ያስታወቁት።

ያም ሆኖ አሁንም ቢያንስ ለአንድና ለሁለት ዓመት ያክል በዚሁ ጉዳይ ላይ አበክሮ በመሥራት በዚህ ረገድ የተገኘውን ለውጥ ለማስቀጠል እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም