በተሽከርካሪ አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት አለፈ

31

አምቦ፣ ሰኔ 28 ቀን 2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጀርሳ ለፎ ወረዳ ቢቴ ቀበሌ ልዩ ስሙ ኪሞዬ በተባለ አካባቢ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

አደጋው የደረሰው ትናንት ቀን ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ላይ 13 ሰዎችን አሳፍሮ ከጊንጪ ከተማ በመነሳት ወደ አዲስ አበባ ይጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 - 66394 (ኦሮ) ሚኒባስ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 - 04933 (አ.አ) ከሆነ አይሱዙ ተሸከርካሪ ጋር በመጋጨቱ ነው።

የኤጀርሳ ለፎ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የትራፊክ ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር ስለሺ ኩምሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአደጋው በሚኒባስ ውስጥ ከነበሩት ውስጥ አሽከርካሪውን ጨምሮ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት አልፏል።

የአይሱዙ አሽከርካሪን ጨምሮ በአምስት ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በአምቦ ሆስፒታል የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ኢንስፔክተር ስለሺ ተናግረዋል።

የአደጋው መንስኤ በመጣራት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም