ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ መርጣ አሸነፈች፤ ታሪካዊ ድልም ተቀዳጀች!

ዴሞክራሲ የብዙዎችን ደጃፍ ያንኳኳል። የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ዘዬ ከታላቋ አሜሪካ እስከ ጀማሪ አገር መስራቾች ስለ ስሙ 'ይነሳሉ ይወድቃሉ'። ለዚሁ ከሁለት ምዕተ ዓመታት (እስከ 500 ዓመታትም የሚወስዱት አሉ) በላይ የዘለቀ አስተዳደራዊ ስርዓት ዘዬን በየአገሮች ለማስፈን ሲባል አያሌ ውጣ ውርዶች ታልፈዋል። ከአቴናውያን ዴሞክራሲ እስከ ሮማን ሪፐብሊክ፤ ከኢጣሊያን ሪፐብሊክ እስከ ታላቋ አሜሪካ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሥርዓት መልኩን እየቀያየረ ተሞክሯል። ሆኖም አስተዳደራዊ ዘይቤው በተቃርኖ የተሞላ እንደሆነ ይነገርለታል። በንድፈ ሃሳብ ከሚተነተንለት እጅግ የገዘፈ ውስብስብ ነገሮችን አቅፎ የያዘም ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዕውቅና ከሰጣቸው ከ193 በላይ የዓለም አገራት ውስጥ 123 የሚሆኑት ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ለመዝርጋት ደፋ ቀና ሲሉ ይስተዋላል። ሆኖም የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ዝቅተኛ መስፈርት አሟልተው የአስተዳደር ስርዓቱን ለመገንባት የሞከሩት ከግማሽ እንደማይበልጡም ይገመታል፤ ይህ እውነታ ሲጤን የዴሞክራሲ አስተዳደር ዘዬን ለማስፈን ምን ያህል ውስብስብ መሆኑን አመላካች ነው። በተለይ ደግሞ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በዓለም ላይ መስፋፋቱም ይነገራል። የአገራት የፖለቲካዊ መስተጋብር ባሕልም ለዴሞክራሲ እያጋደለ መምጣቱም እንዲሁ ተደጋግሞ ይወሳል። ነገር ግን አሁንም ዴሞክራሲ ጽኑ መሰረት ላይ አለመሆኑን በርካታ ማሳያዎች አሉ። ይህ ለምን ሆነ? ዘመናት የተሻገሩ መላምቶች መሰንዘር ይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን የጉዳዩን ውስብስብነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነጥብ ነው።

እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም ገደማ በፍሬድሪክ ኤበርት ስቲፍቱንግና አጋሮች የታተመው መጽሐፍ፤ 'ዴሞክራሲ ምንድን ነው?' ሲል ይጠይቃል። በዚሁ መፅሓፍ ላይ ዴሞክራሲን በአጭሩ ‘የሕዝብ መንግስት ወይም የብዙሐን መንግስት’ ይለዋል። ይህኛው ትርጓሜ የአብርሐም ሊንከንን የዲሞክራሲ ትርጉም ጨምቆ ያስቀመጠ ነው። ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የሕዝቦች ነጻነትና መብትን አስተሳስሮ የያዘ ስልት ነው። ምርጫ፣ የሕግ የበላይነት፣ የስልጣን ክፍፍል፣ ፓርላማ፣ ዴሞክራሲያዊ ብዛሐነት፣ የመንግስትና ተቃዋሚ ተፎካካሪ ቡድኖች መኖር፣ ነጻ ሕዝብና የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት የመፈጠር እውንነት ዋና ዋና የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ምሰሶዎች መሆናቸው በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ ተጠቅሷል። 

'ፒው የጥናት ማዕከል' እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም ዴሞክራሲ ተመራጭ የአስተዳደር ዘይቤነቱ የበለጠ ጠንክሯል ብሏል። ወትሮ ለዚህ አሰተዳደር ስርዓት ጆሮ 'ዳባ ልበስ' ብለው የቆዩ ቱርክና ፓኪስታንን ጨምሮ አብዛኞቹ የዓረብ አገሮች ፍላጎት እያሳዩ መጥተዋል በማለት ነው ጥናቱን ዋቢ በመጥቀስ የሚሞግተው።

የጥናት ማዕከሉ ዳሰሳ እንደሚያመለክተው ጆርዳናውያን፣ ቱርኮች፣ ቱኒዚያዊያን፣ ግብጾችና ሊባኖሳውያን ዜጎች ከ61 እስከ 81 በመቶ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንደሚሹ ተመላክቷል። ይህን እንደማሳያ እንጥቀሰው እንጂ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንደሚመኙት በቀላሉ የሚመጣና የሚጸና አይደለም። ብዙ ውጣ ውረዶች፣ ጠንካራ አሰራርና ጽኑ ሕዝብ ይፈልጋል።

በመሰረቱ ጭልጥ ያሉ አምባገነን የዓለም መሪዎች ጭምር 'ዴሞክራሲ፤ ዴሞክራሲ' ሲሉ ይስተዋላል። አብዛኞቹ ከምዕራባውያን  የሚመጣ ጫና ለመቋቋም ሲሉ፤ ዳረጎት ላለማጣት፣ ከስልጣን ሲውረዱ መጠጊያ፤ መሸሸጊያ እንዲያገኙ፤ ስለ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር አብዝተው ያወራሉ፤ ይሰብካሉ። እውነታው ግን 'ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ነው' የሚሉት ነው። ገዥዎቹ የሚያወሩት ሌላ የሚተገብሩት ሌላ ነው። በዚህ ሳቢያም ያለ ይሉኝታ በሕዝባቸው ላይ ይቆምራሉ። የዚህ ዓይነቱ ተግባር ኢትዮጵያን እንደ አገር ሲፈትናት የቆየ መሆኑም እሙን ነው። በተለይም በ'ኢህአዴግ' የመሪነት ዘመን ይህ ሁኔታ በገሃድ የተስተዋለ ነበር። ፓርቲው የሚመራው መንግስት 'ልማታዊ ዴሞክራሲ' የሚል ስያሜ የተሰጠው የአስተዳደር ዘይቤ ጭንብሉ ሲገለጥ ውስጡ አፋኝና  'ጠቅላይ፤ አግላይ' ስርዓት እንደነበረ ብዙዎች የመሰከሩለት የትናንት ትውስታችን ነው።

የሆነው ሆኖ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ከሚጸናባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ ምርጫ ነው። ዋና ዋናው ለዴሞክራሲያዊ አስተዳደር አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ መንገዶች ውስጥ አንዱ ፍትሐዊና ነጻ ምርጫ ጊዜውን በጠበቀ መልኩ ማከናወን መቻል ነው። ምርጫ ብቁ ዜጎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፤ ፖለቲካዊ ውሳኔያቸውን የሚገልጹበትና መሪያቸውን የሚለዩበት መንገድ ነው። እንደሚታወቀው በሰለጠነው ዘመን ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚተገበረው በተወካይ በኩል ነው። ለዚህ ደግሞ ቀላሉ መንገድ ሕዝቦች ወኪላቸውን እንዲመርጡ ማድረግ ነው። ወኪሎችም ለመረጣቸው ሕዝብ ይታመናሉ፤ ተጠያቂነትም አለባቸው።

የምርጫ ሒደት በብዙ መንገድ ሊከወን ይችላል። በኢትዮጵያም አምስት ዓይነት የምርጫ ስልቶች ይተገበራሉ። እነዚህም ጠቅላላ ምርጫ፣ የአካባቢ ምርጫ፣ የማሟያ ምርጫ፣ ዳግም ምርጫና ሕዝብ ውሰኔ (ሪፈረንድም) ተብለው ተለይተዋል። እነዚህን ምርጫዎች የሚያስተባብር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደግሞ በሕግ አግባብ ተቋቁሞ በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት ምርጫን ያስተባብራል፤ ይመራል። ታሪክን መለስ ብለን ስንመለከት ኢትዮጵያ ከአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ 12 ምርጫዎችን አካሂዳለች። እነዚህም በንጉሱ ጊዜ አምስት፣ በደርግ አንድ፣ በኢህአዴግ አምስት እንዲሁም አሁን  በብልጽግና አንድ ምርጫ አካሒዳለች። የምርጫዎቹን ዴሞክራሲያዊ ሒደቶች ለጥናትና ምርምር እንተወውና መቼታችንን የዘንድሮ ምርጫ ላይ ባመድረግ አንዳንድ ነጥቦች እናንሳ።

ከሁሉም አስቀድሞ የቀድሞ ቅድመ ምርጫ ወቅቶች ሂደቶችና ዓይነቶች ምልከታና አነስተኛ ቅኝት እናድርግ። በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) መሪነት ኢትዮጵያ አምስት ምርጫዎችን አድርጋለች። በ1987፣ በ1992፣ በ1997፣ በ2002ና በ2007 ዓ.ም በተከታታይ ምርጫ አድርጋለች። ከ1997ቱ ምርጫ በስተቀር በሁሉም ምርጫዎች ገዢው ፓርት ኢህአዴግ ከ98 በመቶ በላይ ምርጫውን አሽንፎ የተሟላለት ምርጫ ማካሄዱን በልሳኖቹ ሲደሰኩር ሰንብቷል። ብዙሃኑ ምርጫዎቹ 'የይስሙላ' ናቸው ይሏቸዋል።

በ2007ቱ ምርጫ ኢህአዴግ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ያሉትን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮች በሙሉ ማለትም (547ቱንም) አሽንፏል። በዚህ ምርጫ አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ የምክር ቤት መቀመጫ ያላገኘበት  ሆኖ በታሪክ ተሰንዷል። ይህም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምርጫው ማግስት ጀምሮ መንግስትን ወደ መታገል እንዲገባ ከአደረጉት ምክንያቶች ውስጥ የሚጠቀስ ነው። ጉዳዩ እየተፋፋም ከ2008 ዓ.ም በኋላም በየቦታው ሕዝባዊ እንቢተኝነቱ እየተቀጣጠለ ሄደ። በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አምጽ ሁለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን እስከማሳወጅ ደርሶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ክስተቱ እየተባባሰ መጥቶ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከድርጅቱ ሊቀ መንበርነትም ሆነ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ በገዛ ፍቃዳቸው ለቀቁ።ይህን ተከትሎም መጋቢት 2010 ዓ.ም ዶክተር አብይ አሕመድ የደርጅቱን ሊቀ መንበርነትና የጠቅላይ ሚኒስትርነት በትረ ስልጣን ተረከቡ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በመጀመሪያ የፓርላማ ንግግራቸውም ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን የእውነት ተግባራዊ ለማድረግ ቃል ገቡ፤ የፖለቲካ ምህዳሩንም ለማስፋት እንደሚሰሩ ይፋ አደረጉ።

ከዚያን ወቅት ጀምሮ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የዘመነና የዴሞክራሲ ሽታ የሚታይበት ይሆን ዘንድም በእስር ላይ  የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እንዲፈቱ ተደረገ። በውጪ አገር ተደብቀው ሲታገሉ የቆዩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ወደ አገር ቤት ተመለሱ። ከዚህ ባለፈም በሽብርተኝነት የተፈረጁ ድርጅቶችም ስያሜያቸው እንዲነሳ ተደረገ። የወቅቱ የፖለቲካ ግለት እየተሟሟቀ በመሔዱም ሕዝቡ ከፊት ያለውን ምርጫ በጉጉት እንዲጠብቅ አደረገው። መንግስትም ምርጫውን ለማሳለጥ የሚረዱ ገለልተኛ ተቋማት ማዘጋጀቱን ጎን ለጎን ማስኬድ ጀመረ።

ነጻና ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ ምስረታ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 102 መሠረት የተቋቋመ ገለልተኛ ሕገ-መንግሥታዊ ተቋም ነው። ቦርዱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የፌዴራል እና የክልል ጽህፈት ቤቶችን ያደራጀ ሲሆን፤ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ደረጃ ቢሮዎች እንዲኖሩት ተደረገ። የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም አምስት አገራዊ ምርጫ ያስፈጸመ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ ሁለት የአካባቢ ምርጫና ስድስት ሕዝበ ውሳኔዎችን አደራጅቷል።

የቀድሞው ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነትን፣ ነጻነት፣ ተአማኒነትና ቅቡልነት ያለገኝ በመሆኑም ቦርዱን ዳግም የማቋቋም እንቅስቃሴ ከ2011 ጀምሮ ሲደረግ ቆይቷል። በአዋጅ 1133/2011 መሠረት ዳግም ለተደራጀው ቦርድ የተሰጡ ሥልጣንና ተግባራት የሚከተሉትን ይመስላሉ። እነዚህም በሕገ መንግሥቱና በምርጫ ሕግ መሠረት የሚካሄድ ማንኛውም ምርጫና ሕዝበ ውሳኔ በገለልተኝነት ማስፈፀም፤ የመራጮች ትምህርት ለሚሰጡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ መስጠት፤ መከታተልና መቆጣጠር፤ የፖለቲካ ድርጅቶችን መመዝገብ፣ በሕጉ መሠረት መከታተልና መቆጣጠር፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግበትን መስፈርት ማውጣትና በዚሁ መሠረት ድጎማውን ማከፋፈል፤ በምርጫ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም መወሰን፤ የምርጫ ክልሎችን አከላለል በተመለከተ ጥናት አድርጎ ለፌደሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳብ ማቅረብ የሚሉት ይገኙበታል።

ከዚህ ባለፈም ከምርጫና ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ማሰባሰብ፣ ማጠናከር፣ የምርጫ ህጎችንና አፈጻጸምን በመገምገም ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮችን ለይቶ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ፤ የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ መድረክን ማስተባበር፤ የምርጫው ውጤቶችን ማረጋገጥና ይፋ ማድረግ፤ በምርጫ ሂደት ለሚቀርቡ ቅሬታዎች አስተዳደራዊ መፍትሄ መስጠት፤ በምርጫ ሂደት የምርጫ ውጤትን የሚያዛንፍ የህግ ጥሰት ተከስቶአል ብሎ ሲያምን ውጤቱን መሰረዝና ድጋሚ ምርጫ ማካሄድ እንዲሁም በምርጫ ሂደት የተፈጸመ የህግ መጣስ፣ ማጭበርበር ወይም የሰላምና ፀጥታ ማደፍረስ ድርጊት የፈፀሙ ግለሰቦችን በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ፤ በጀት አዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማቅረብ፣ የማጸደቅና በሥራ ላይ የማዋል፤ በየደረጃው የሚካሄዱ ምርጫዎችን መርሀግብር ሰሌዳ እንዲዘጋጅ የማድረግ፣ የማጽደቅ እንደ አስፈላጊነቱ የማሻሻልና መፈጸሙን የመከታተል፤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የማቅረብ፤ በዚህ ህግና በሌሎች ህጎች የተሰጡትን ኃላፊነቶች ለመወጣት አስፈላጊ የሆኑ ማንኛውንም ተግባራትን የማከናወን ኃላፊነትና ስልጣን ተሰጥቶታል።

እንግዲህ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ነጻና ገላልተኛ ተቋማትን ከማደራጀት ይጀምሯል። በተለይ ደግሞ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ግንባታ ምሰሶ የሆነው ነጻ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄድ ዋነው ጉዳይ ነው። ለዚህ ነው ኢትዮጵያ ይህን ተቋም ዳግም ማደራጀት ያስፈለጋት። የተቋሙን ስልጣንና ተግባር ማሻሻልና ማጠናከር ብቻ ሳይሆን ማን ይምራው የሚለውም በአግባቡ የተጤነ ነበረ። ለዚህም የቀድሞ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ መሪ የነበሩትንና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት በመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ፤ የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው ያገለገሉና  በኋላም በስደት በውጭ አገር ለዓመታት የቆዩት ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ተቋሙን ለመምራት ብቁ መሆናቸው ታምኖበት ቃለ መሐላ ፈጸሙ፤ ሌሎች ብቃት ያላቸው የቦርድ አባላትም ተመርጠው ቦርዱን በመምራት ተሳታፊ ሆኑ። ይህ ሁሉ 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተሻለ እንዲሆን የተካሔደ ዝግጅት ስራ አድርጎ መውሰድ ይቻላል።

ወይዘሪት ብርቱካን በ2012 ዓ.ም ላይ ይካሄዳል ተብሎ ቀን ለተቆረጠለት ምርጫ ቦርዱ በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት ስራቸውን ማከናወን ጀመሩ። በቅድመ ምርጫ ስራውም ከተከናወኑ ተግባራት  አንዱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአዲስ መልክ እንዲመዘገቡ ማድረግ ነበር። በዚህ ወቅት በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ መሰረት ከነበሩት 117 ፓርቲዎች መካከልም ትክክለኛውን መስፈርት ያሟሉት 52ቱ ብቻ ነበሩ። ቦርዱ እነዚህን ድርጅቶች ይዞ ለምርጫው እየተዘጋጀ ባለበት ሁኔታ የኮቪድ 19 ዓለም ዓቀፍ ወረርሺኝ ኢትዮጵያን መናጥ ጀመረ። በዚህ ሳቢያም አገሪቷ ለማከናወን ያቀደቻቸው በርካታ ተግባራት መታጠፍ ግድ ሆነ፤ ታጠፉ። ትምህርት ቤቶች ተዘጉ። ስራዎች ተስተጓጎሉ። ይህም ሁኔታ ምርጫውም እንዲራዘም ምክንያት ሆነ።

በወቅቱ ምርጫው መራዘሙን አሰምልከቶ ቦርዱ የሚከተለውን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ።‘’የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2012 ዓ.ም የሚካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ ለማስፈፀም የቅድመ ምርጫ ዝግጅት ስራዎች ሲያከናውን ከቆየ በኋላ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን ይፋ አድርጓል። በዚህ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫው ነሐሴ 23 ቀን 2012 እንዲካሄድ ተወስኖ ቦርዱ በጊዜ ሰሌዳው የተገለጹ ተግባራትን በተያዘላቸው ጊዜ እያከናወነና ለህዝብ እያሳወቀ እንደቆየ ይታወሳል። በዚህም መሰረት በያዝነው መጋቢት እና በሚያዚያ 2012 ዓ.ም መጠናቀቅ ያለባቸው በርካታ ስራዎች አሉ። ከነዚህም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የመራጮች ምዝገባ፤ የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላ፤ ስልጠናና ስምሪት፤ የመራጮች ትምህርት ምዝገባ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ስርጭት የመሳሰሉት ናቸው። እነዚህን ስራዎች በጊዜ ሰሌዳው መሰረት ለማከናወን ቦርዱ ተገቢ ጥረት እያደረገ ቢሆንም በአገራችን እና በአለም ላይ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንቅስቃሴዎች እንዲቋረጡ አስገድዷል” በማለት አሳወቀ።

በዚህ መሐልም የትግራይ ክልል 'ወረርሽኙን እየተካላከልኩ ምርጫውን ማድረግ እችላለሁ' በሚል የተለየ

ሀሳብ ይዞ ብቅ አለ። ምርጫ ቦርድም “. . . 6ኛውን አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ቀደም ሲል ቦርዱ ባወጣው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ማካሄድ የማይቻል መሆኑን ወስኖ ይህንኑ ውሳኔ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም የቀረበለትን የቦርዱን ውሳኔ ተቀብሎ የህገ-መንግስት ትርጉም እንዲሰጥበት መወሰኑ ይታወሳል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ ምርጫውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የህዝብ ጤና ስጋት ሆኖ ባለበት ሁኔታ ማካሄድ የማይቻል በመሆኑ የፌዴራልና ክልል ምክር ቤቶች የስልጣን ዘመን እንዲቀጥል እንዲሁም አጠቃላይ ምርጫው ስልጣን ያላቸው አካላት ወረርሽኙ የህዝብ ጤና ስጋት አለመሆኑን ካረጋገጡበት ጀምሮ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ እንዲካሄድ ወስኗል” በሚል አሳወቀ፤ ክልሉ ግን አሻፈረኝ ብሎ ሕገ ወጥ ምርጫ ማድረጉ ይታወሳል። 

ቦርዱም የሁኔታዎች መለወጥና የወረርሽኙ ጉዳይ የተሻለ መሆኑን ተከትሎ በ2013 ዓ.ም ዳግም የምርጫ ዝግጅት ማድረግ ጀመረ። በዚህም መሰረት ቀደም ብሎ መስፈርት አሟልተው ምዝገባቸው የተጠናቀቀ እና በሂደት ላይ ያሉ ፓርቲዎችን ዝርዝር አሳወቀ። ቦርዱ ከዚህ ቀደም ውሳኔ ያልሰጠባቸው እንዲሁም የተጠየቁትን ማብራሪያዎች ያቀረቡ ፓርቲዎችን አስመልክቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል። "አፈጻጸሙ በተጀመረው የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ መሳተፍ የሚችሉት ፓርቲዎች በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፉት 52 የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆናቸውን ቦርዱ ያሳውቃል። ምርጫውን ለመሳተፍ ቅቡልነት ያላቸው ሂደቱን አጠናቀው የጨረሱ ፓርቲዎች መሆናቸውን ያሳውቃል።'' ቦርዱ በግልጽ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን ይፋ አድርጎ ምርጫውን ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ለማድረግ ቀን ቆረጠ። ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫው ወደ ሰኔ 14 ተዘዋዋረ፤ በአብዛኛው የአገሪቷ አካባቢዎችም በዚሁ ዕለት ምርጫ ተካሔደ።

ስድስተኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ በተለዋወጭ ጉዳዮች ውስጥና ብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ ሆኖ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የመጀመሪያው ዙር ፍጻሜ አገኘ።

የምርጫ ኡደት

ምርጫ የአንድ ጊዜ ክስተት ሳይሆን ኡደት የሚመስል ሂደት ያለው ተግባር ነው። ጊዜውን ጠብቆ ይካሄዳል። ቅድመ ምርጫ፣ ምርጫና ድሕረ ምርጫ ተብሎ በሶስት ምዕራፍ ይካሄዳል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በዚሁ አካሄድ መሰረት እያንዳንዷን ሂደት አልፎ ድሕረ ምርጫ ላይ ደርሷል። ለመሆኑ በየሂደቶቹ ምን ምን ስራዎች ታለፉ፤ በጨረፍታ እንየው። 

ቅድመ ምርጫ

ቅድመ ምርጫ፣ ከድምፅ መስጫ ቀን በፊት ያለው ጊዜን ያጠቃለለ ነው። አብዛኛው የምርጫ እንቅስቃሴ የሚከናወንበት ወቅት ይህው ነው። በቅድመ ምርጫ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጅት እና ምዝገባ፣ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ፣ ሥልጠና እና ምደባ፣ የምርጫ ክልልን የማካለል፣ የመራጮች ምዝገባ፣ የፆታና የብዙሃን ማኅበራት አሳታፊነት፣ የሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት፣ የምርጫ ጣቢያ አደረጃጀት፣ የዕጩዎች ምዝገባ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳ፣ የብዙሃን መገናኛዎች የሥራ እንቅስቃሴዎች በስፋት እና በጥልቀት የሚካሔዱበት ወቅት ነው። ይህ ወቅት በምርጫ አስፈጻሚው ተቋም እንዲሁም በሌሎች ባለድርሻ አካላት መጠነ ሰፊ ዝግጅት የሚደረግበት ነው። በዚሁ መሰረት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተገቢ ሂደቶችን አልፏል።

ቦርዱ የገለልተኛ ምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላን በስፋት አከናውኗል። በመጀመሪያ ዙር 140 ሺ በላይ በአስፈጻሚነት የሚሰሩ ግለሰቦችን አዘጋጅቶ ገለልተኝነታቸውን የማጣራት ስራ አከናውኗል። በጥቅሉ 138 ሺ 655 የምርጫ አስፈጻሚዎች አዘጋጅቶ ነበር። በኋላ ላይም ለምርጫው ዕለትም የተሳለጠ ስራ ለማከናወን ሲባል ተጨማሪ 106,345 ምርጫ አስፈጻሚዎችን መልምሎ አሰልጥኗል።

ከምልመላው ጎን ለጎን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለድምጽ መስጫ ቀን ስራቸውን የሚያከናውኑ ሁሉንም የምርጫ አስፈጻሚዎች አስልጥኗል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል አሰልጥኖ ለምርጫው ዝግጁ ማድረግ ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ መገመት አይከብድም። ይህም ዴሞክራሲያን ለማጽናት የተደረገ ጅምር ነው ማለት ይቻላል።

በአጠቃላይ ለስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ 673 የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። 49 ሺህ 407 የምርጫ ጣቢያዎችም ዝግጁ ነበሩ። የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች ከትግራይ ክልል በስተቀር በዘጠኙም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ተደራጅተው አስፈላጊ ዝግጅት ተደርጓል። ምርጫው በተቃረበበት ወቅት በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የሶማሌና ሀረሪ ክልሎችን ጨምሮ የተወሰኑ የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች ምርጫው በጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲደረግ መወሰኑ ይታወሳል።

ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ተወዳዳሪዎች እጩዎች ምዝገባ በቂ ጊዜ ተሰጥቶት ተከናውኗል። በዚህም 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎችን ያስመዘገቡ ሲሆን፤ በግል የተወዳደሩ 125 እጩዎች ተመዝግበዋል። በመራጭነትም ከ37 ሚሊዮን በላይ መራጮች ተመዝግበው ካርድ ወስደዋል።

በምርጫ ወቅት

በምርጫ ዑደት መሠረት፣ በምርጫ ወቅት፣ በርካታ ወሳኝ ተግባራት የሚከናወኑበት ነው። የድምፅ አሰጣጥ፣ ቆጠራ፣ ውጤት አገላለጽ እና ማረጋገጥ ይካሄዳሉ። እንዲሁም፣ የቅሬታ አቀራረብ እና አፈታት በዚህ ምዕራፍ የሚካተቱ ተግባራት ናቸው። 

የምርጫው እለት! ሰኔ 14 ምን እንደሚመሰል ቅኝት እናድርግ።

ቀኑ ያለ ማገነን ሕዝቡ በነቂስ የወጣበት ምርጫ ነበር ማለት ይቻላል። በእለቱ በሁሉም አቅጣጫ የሚገኙ ኢትዮጵያውን መራጮች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ቀጣይ አስተዳዳሪያቸውን ለመምረጥ ማልደው ነበር የተነሱት። በአብዛኛው የምርጫ ጣቢያዎች መራጮች ከንጋት 12 ሰዓት በፊት ሰልፍ ይዘው የምርጫውን መጀመር ይጠበባቃሉ። ንጋት የጀመረው የምርጫ ሂደት እስከ ምሽት 3 ሰዓት ተራዝሟል። ይህም አልበቃ ብሎ ሰልፍ ይዘው ለመምረጥ የሚጠባበቁትን ዜጎች ማስተናገድ ተገቢ በመሆኑ እስከ ምሽት ሰባት ሰዓት ድምጽ የተሰጠበት ምርጫ ጣቢያ እንደነበርም ይታወቃል።

እስኪ ለአብነት የአንድ ምርጫ ጣቢያ ቅኝቴን ላጋራችሁ ። ጠዋት ሁለት ሰዓት ተኩል ጉለሌ ክፍለ ከተማ፤ አዲሱ ገበያ ምርጫ ጣቢያ 10-11። በዐለቱ በሁለት ሰዓት ተኩል በሁለቱም ጣቢያዎች ረጃጅም ሰልፎች በሁለትና በሶስት ረድፍ ይስተዋላል። መራጮች በጽናት ቆመው ተራቸውን ይጠብቃሉ።

በሰልፍ ላይ ከወጣቶች ጀምሮ በሰው፣  በከዘራ የተደገፉ አዛውንትና የዕድሜ ባለጸጋዎች ይገኙበታል። ወንዶችም ሴቶችም በነቂስ የወጡበት የምርጫ ጣቢያ ነበር። ሁሉም መራጮች በሚባል ደረጃ በፊታቸው ላይ እርጋታ ይነበባል። የምርጫ አስተባባሪዎቹም ዘና ብለው ስራቸውን ይከውናሉ ። በምርጫ ጣቢያው በቆየሁባቸው ሁለት ሰዓታት ገደማ ሰዎች ለመምረጥ በትንሹ ከአንድ ሰዓት ተኩል እስከ ሁለት ሰዓት ድረስ መጠበቅ ይኖርባቸው የግድ ነበር።

ያኔ ነው! የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም ሳይበግረው መሪውን መርጧል የሚለው ሀሳቤ ገዝፎ የተሰማኝ። ብዙዎች ያሟረቱበትን፤ኢትጵያውያን በራሳቸው በመተማመን ያለምንም ኮሽታ ምርጫውን አካሂደዋል። ሟርተኞችም አፍረዋል። ለወዳጅ ጠላቶችም ሁነኛ መልዕክት የተላለፈበት ታሪካዊ ምርጫ ሆኖም አለፏል። ለዚህም ኢትዮጵያውያን ያለልዩነት ደስታቸውን ገልፀዋል። ቀጣዩንም በተስፋ እየተጠባበቁ ይገኛሉ። አሁን ላይ የሁሉም ምኞት ‘ቸር ያሰማን ሆኗል’።

ከምንም በላይ በታሪካችን ያልተለመደውና በዘንድሮው ምርጫ የታየው ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየምርጫ ጣቢያው የተለጠፈውን ውጤት የተረዱበትና ያስተላለፉት መልዕክት ለአገራችን ታላቅ የምስራች ነው። ፖለቲከኞቹ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈዋል። ከነዚህ መካከል አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ግርማ ሰይፉ ይገኙበታል። ''ኢትዮጵያ እንድታሽንፍ ስርተን ምርጫው በሠላም ተጠናቋል! ለብሽሽቅ ጊዜ የለንም! ያመንበትን ሰርተናል ውጤቱን በዝርዝር ገምግመን አስተያየት እንሰጣለን። በርግጠኝነት ለብሽሽቅ ፍላጎት ካላቸው ያነሰ ድል አላገኘንም። 'ዜጎች ይመርጣሉ፣ ኢትዮጵያ ታሽንፋለች!' ብለን ሠርተናል። ይህ ድል የሠላም ወዳዶች እንጂ የጠብ ጠንሳሾች አይደለም።'' ሲሉ ገልፀውታል።

ሌላው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጣሒር መሐመድም ይህን ብለዋል። ''የግላችን ነገር ሙሉ ነው ፤ የጎደለው በህዝባችን በኩል ያለው ነው በሚል ሞክረናል። ሰላም ልማት እና ማህበራዊ እረፍት ለህዝባችን እመኛለሁ። ሳላደርገው ወይም ባይሆን ኖሮ ብዬ የሚቆጨኝ የለም!!'' 

በምርጫ ማግስት ጀምሮ ጠብጫሪ መግለጫዎች ላይ የሚያተኩሩት ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ስክነትን መርጠዋል። ወደ መገናኛ ብዙሃን ብቅ ያሉትም ለሰላምና ለአንድነት ቅድሚያ የሚሰጡ መሆኑን ደጋግመው እየገለጹ ነው። ይህ ይበል የሚያሰኝ ክሰተት ነው። መጨረሻውም በዚሁ እንደሚቀጠል ተስፋ ይደረጋል።

ድኅረ ምርጫ 

የድህረ ምርጫ፣ የተሰጠው ድምጽ ቆጠራ ተከናውኖ የምርጫ ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላ ያለው ጊዜ ነው። በዚህ ወቅት፣ የድህረ ምርጫ ግምገማ፣ በህጋዊ ማዕቀፎች መሠረት የምርጫ ክልል ማካለል እና የተቋሙን ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ዝግጅት እና የመሳሰሉትን ሰፊ ሥራዎችን ያካትታል። በዚሁ መሰረት ምርጫ ቦርድ ምርጫ ያልተካሄደባቸው አካባቢዎች ማለትም የትግራይ ክልል እንዳለ ሆኖ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የተወሰኑ አካባቢዎች፣ ሶማሌና ሀራሪ ሙሉ ለሙሉ፣ ኦሮሚያ ጥቂት ቦታዎች፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችና እንዲሁም አማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚደገም ይጠበቃል።

ዘንድሮ በተካሔደው ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋነቱንና ሕገ አክባሪነቱን በገሃድ አሳይቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ምን ያህል ለዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ዘይቤ ቀነኢ እንደሆኑም አሳይተውበታል። በዚህ በውስጥም በውጪም በርከት ያሉ ጫናዎች ባለቡት ወቅት እንዲህ በአንድነትና በሕብረት መቆሙም አስደናቂ ነው። 

እውነት ነው፤ ኢትዮጵያ መርጣ አሽንፋለች፤ ላቅ ያለ የድል ታሪክም ተቀዳጅታለች። በዚህ ተግባሯ ባዕዳንንም ሆነ ባንዳዎችን አንገት አስደፍታለች። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም