የሱዳን ህዝብ ስለ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሃይል ማመንጫ እውነታውን ሊገነዘብ ይገባል --አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ - ኢዜአ አማርኛ
የሱዳን ህዝብ ስለ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሃይል ማመንጫ እውነታውን ሊገነዘብ ይገባል --አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ
ሰኔ 27 / 2013 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አንድ የኃይል ማመንጫ ግድብ እና ጉዳዩም ቴክኒካዊ ቢሆንም ከሚገባው በላይ የመነጋገሪያ እና የፖለቲካ ጉዳይ እየሆነ በመምጣቱ የሱዳን ህዝብ እውነታውን ሊገነዘብ ይገባል ተባለ።
በሱዳን ለሚገኙ ጋዜጠኞች የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ በሱዳን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደር ይበልጣል በመግለጫቸው “የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አንድ የኃይል ማመንጫ ግድብ እና ጉዳዩም ቴክኒካዊ ቢሆንም ከሚገባው በላይ የመነጋገሪያ እና የፖለቲካ ጉዳይ እየሆነ በመምጣቱ ወንድም ለሆነው የሱዳን ህዝብ እውነታውን እንዲያውቅ ለማገዝ የተዘጋጀ ጋዜጣው መግለጫ ነው” ብለዋል።
የአባይ ተፋሰስ የኢትዮጵያን ሁለት-ሶስተኛ የውሃ ሀብት የሚሸፍን እንዲሁም የናይልን 86 በመቶ ኢትዮጵያ የምታበረክት ቢሆንም ሀብቱ እያለ እስካሁን ድረስ 65 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በኤሌክትሪክ እጦት በጨለማ ውስጥ ይኖራሉ ያሉት አምባሳደሩ፤ አባይን ማልማት ለኢትዮጵያ መብቷ እና ግዴታዋ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ስትጠቀም ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ በመሆኑም በማንም ተጋሪ ሀገር ላይ ጉልህ ጉዳት እንደማታደርስ ፣ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግንና መርህን አክባሪ እንደሆነችና ኢትዮጵያ የፍትህና የእውነት ሀገር መሆኗንም የተመሰከረላት ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን፣ የጋራ ታሪክ ያላቸው ዕጣፈንታቸውም የተሳሰረ መሆኑን ያስረዱት አምባሳደር ይበልጣል በታሪክ እንደታየው አንዳቸው ለአንዳቸው ጋሻ ሆነው መቆየታቸውን አውስተዋል።
ከዚህ አንጻር ሱዳን ለኢትዮጵያውያን የክፉ ቀን መጠጊያ እንደሆነችው ሁሉ ኢትዮጵያም ለሱዳን ሰላም፣ መረጋጋት እና አንድነት የቁርጥ ቀን ደራሽ መሆኗን አስታውቀዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም ያለው በመሆኑም ሱዳናዊያን እና የሱዳን መንግስት ለግድቡ ግንባታ አስፈላጊውን የፖለቲካ፣ የማቴሪያልና የሞራል ድጋፍ ሲያደርጉ እንደቆዩ ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ግድቡ “የሱዳን ኃይል ማመንጫ ግድቦች ዓመቱን በሙሉ አቅማቸው ኃይል ለማመንጨት እንደሚረዳ፣ የአባይ ወንዝ ተመጣጣኝ ፍሰት ስለሚኖረው በዓመት ሶስት ጊዜ ለማምረትና ምርታማነትን እንደሚጨመር፣ ወንዙ በበጋ ወቅት ከነበረው ከሁለት እስከ አራት ሜትር ከፍ እንደሚል እና ዓመቱን ሙሉ የተመጠነ ፍሰት ስለሚኖረው ለመጓጓዣነት (navigation) የተሻለ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር፣ በወንዙ የውሃው ከፍታ ስለሚጨምር ለውሃ መሳቢያ ሞተሮች /pumps ወጪን እንደሚቀንስ፣
ወደ ሱዳን ግድቦች ይገባ የነበረውን 90% ደለል በመቀነስ ሱዳን ለደለል ማስወገጃ በየዓመቱ የምታወጣውን 50 ሚሊዮን ዩሮ እንደምታድንና ሱዳን በአነስተኛ ዋጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ማግኘት እንደምትችል፣ ጠቅሰዋል።
የጎርፍ አደጋ ሙሉ በሙሉ በማስወገድ የህይወትና ንብረት ጥፋትን እንደሚታደጋት አምባሳደር ይበልጣል ገልጸዋል።
ግድቡ ለሱዳን የሚሰጠው ጥቅም አሁን በስልጣን ላይ ያሉትን ጨምሮ በሱዳን ባለሙያዎች ጥናት የተረጋገጠ ሆኖ ሳለ “ለ20 ሚሊዮን ሱዳናዊያን እና ለሱዳን ግድቦች አደጋ ነው” መባሉ ከእውነት የራቀ እንደሆነም ተናግረዋል።
የግድቡን ደህንነት በወቅቱ ያለውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም፣ በጠንካራ የአለት መሰረት፣ ከምንም ዓይነት የመሬት እንቅስቃሴ ነፃ በሆነ አካባቢ፣ ሳይንሳዊ ደረጃውን በጠበቀ ዲዛይን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ግድቦችን በመገንባት ስመጥር በሆነ ኩባንያ እየተገነባ ያለ አስተማማኝ ግድብ እንደሆነ እና የሱዳን የውሃ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ያሲር አባስም የግድቡ ደንነት በሱዳን እና ግብጽ ካሉ ግድቦች የተሻለ እንደሆነ መናገራቸው የዚሁ ማሳያ መሆኑን አምሳደር ይበልጣል ገልጸዋል።
የግድቡን ሙሌት በተመለከተ መቼ ምን ያክል ውሃ መያዝ እንዳለበት በሶስቱ ሀገራት ባለሙያዎች መግባባት የተደረሰበት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
አምባሳደሩ አያይዘውም 86 በመቶ የውሃ ሀብትን ለናይል የምታበርክትን ሀገር በራሷ ግዛት፣ በራሷ ገንዘብ እና የራሷን ፍትሐዊ የውሃ ድርሻ ተጠቅማ ለምትገነባው ግድብ ውሃ አትሙላ ማለት ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።
ጉዳዩ በሶስቱ አገሮች መካከል በሚደረግ ድርድር የሚጠናቀቅ ሆኖ ሳለ፣ ሱዳን እና ግብጽ ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቅም መርሆዎች ባፈነገጠ መልኩ “የኢትየጵያን የውሃ የመጠቀም መብት ለመገደብ መፈለጋቸው፣ ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ እንደሚጥሩ ተናግረው ፤ ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ እምነት አላስፈላጊ ጫና ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ እንደማይችል በአጽንኦት ገልጸዋል።
በመሆኑም በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር በሚደረገው ድርድር ሶስቱን አገሮች ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት መድረስ እንደሚቻል አምባሳደር ይበልጣል መናገራቸውን በሱዳን የኢትዮጵያ ኢምባሲ አስታውቋል።