በዚህ ፈታኝ ወቅት ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን እንቆማለን- በጸጥታው ምክር ቤት የኬንያ አምባሳደር

በትግራይ ክልል ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሰኔ 25 ቀን 2013 ዓ.ም ውይይት አድርጓል። በዚህ ውይይት ላይ የኬንያው ተወካይ አምባሳደር ማርቲን ኪማኒ አስደማሚ ንግግር አድርገዋል። በተመድ የኬንያ ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ማርቲን ኪማኒ ባደረጉት ንግግር “በአፍሪካ ሰላምና ጸጥታ መከበር የአፍሪካ ሃገራትና ህዝቦች በጸጥታው ምክርቤት ጥቅማቸውን ለማስከበር ስለሚኖራቸው አስተዋጽኦ ዙሪያ አንድ አይነት አቋም እንዳለን ለማሳወቅ” እንወዳለን ሲሉ ገልጸዋል። የአፍሪካውያን የሞራል የሃይማኖትና የባህል ልእልና ሊዘነጋ እንደማይገባ ያብራሩት አምባሳደሩ ለአፍሪካም ይሁን ለኢትዮጰያ እያንዳንዱ ሕይወት ዋጋ እንዳለው እንረዳለን ብለዋል።

አምባሳደር ማርቲን በዚሁ ንግግራቸው ባለፉት ወራት በትግራይ የተፈጠረው ግጭት ሲባባስ ሰብአዊ ቀውሱም በዚያው ልክ እያደገ መምጣቱን ግንዛቤ ሊወሰድበት የሚገባ መሆኑን ጠቁመው የኢትዮጵያ መንግስትም እያደረገ የነበረውን የሰብአዊ ድጋፍ አድናቆት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። አምባሳደሩ ሁሉም ሀገራትና አለምአቀፍ ተቋማት በትግራይ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

የጸጥታው ምክርቤት አባላትና የአለምአቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ላደረገችው ምርጫ የእውቅና ቦታ የመስጠት ፍላጎት ባያሳይም የኢትዮጵያ ህዝብን የዴሞክራሲና የሰላም ፍላጎት የምንደግፈው መሆኑን እገልጻለሁ ያሉት አምባሳደሩ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ የጸጥታ የፖለቲካ ችግሮችና ሌሎች ጉዳዮች ባሉበት ሁኔታ የተደረገው ምርጫ የኢትዮጵያንና የዜጎቿን ፍላጎት ግልጽ አድርጎ ያሳየ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ልኡክ ጊዜያዊ ሪፖርት ያመለክታል ብለዋል። “እየተነጋገርንበት ያለው የትግራይ ጉዳይ ለሰላም መስፈን መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን በመገንዘብ ችግሩን ከሚያባብስ እንቅስቃሴ በመቆጠብ ሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቱን በጭንቀት ውስጥ ሆነው ለሚጠብቁ ሰዎች እንዲደርስ በጥንቃቄና በፍጥነት ልንረባረብ ይገባል” ሲሉ ጥሪ ያቀረቡት አምባሳደሩ አለማቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ መንግስት ሰብአዊነትን አስቀድሞ ያደረገውን የተኩስ አቁም ውሳኔ ሊደግፈውና ሊያደንቀው ይገባል ብለዋል። በሁሉም የትግራይ አካባቢዎች በችግር ውስጥ ላሉ ሁሉም ሰዎች የነፍስ አድን እርዳታ እንዲዳረስ የተኩስ ማቆም ውሳኔው ዘላቂና ሁሉም ወገኖች የሚያከብሩት እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው አብራርተዋል።

የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ለማሰናከል ሆን ተብሎ የሚደረግ እንቅስቃሴ የሚወገዝ መሆኑን ያመለከቱት አምባሳደር ማርቲን የተከዜ ድልድይ መሰበሩ እንደሚያሳስባቸውና ክስተቱም ሰብአዊ ቀውሱ እንዲቀጥል የሚደረግ ጥረት አድርገው እንደሚወስዱት ገልጸዋል። ሰብአዊ ድጋፉ እንዲቀጥልና የተኩስ አቁሙ ዘላቂ እንዲሆን ማንኛውንም ወታደራዊ እንቅስቃሴ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚደረጉ ውይይቶችና ንግግሮች ለሁሉም ነገር መፍትሄ እንደሆነ የሚያምኑ ለመሆናቸው ባለፉት ጥቂት አስርት አመታት በአዲስ አበባ የተደረጉና የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ገንቢ ተጽእኖ ያረፈባቸው በርካታ የአፍሪካ የሰላምና ጸጥታ ጥረቶች ማሳያ ናቸውም ብለዋል።

አምባሳደሩ አክለውም ኢትዮጵያም እነዚህን ሰላም የማምጫ ልምዶቿን እንድትጠቀምባቸው ምክረሃሳብ አቅርበዋል። ግጭቱ የኢትዮጵያውያንን  ውድ ህይወት እየበላ በመሆኑ የሰላም ማእከሏ ኢትዮጵያ በአፍሪካዊ መፍትሄዎች ሰላምን ለማምጣት የበኩሏን መወጣት ቢኖርባትም የጸጥታው ምክርቤትም አፍሪካን ለተመለከቱ ጉዳዮች የአፍሪካውያንን መፍትሄዎች መስማት ይኖርበታል ብለዋል። 

የጸጥታው ምክርቤትም ሆነ ሌሎች አባል ሃገራት አፍሪካውያን የሚያደርጓቸውን ጥረቶች መደገፍና ማበረታታት እንዳለባቸው የገለጹት አምባሳደሩ፤ በኢትዮጵያ ተኩስ እንዲቆም በማድረግ የሰብአዊ እርዳታ ስርጭት እንዲፋጠን በመትጋት ንግግር እንዲጀመር እርቅና እውነት እንዲፈለግ መጣር አፍሪካውያን የገነቡትና በአፍሪካ ህብረት የሰብአዊና የህዝቦች መብቶች ኮሚሽን ተቀባይነት ያገኘ መሆኑን አስረድተዋል። አሁን ጊዜው የበሰለ ዲፕሎማሲያዊ ስራ የሚሰራበት ህዝብን ያስቀደመ የእርዳታና የሰብአዊ ድጋፍ ከፍ እንዲል የሚደረግበት እንዲሁም የሀሰት መረጃዎችን ታግለን አካባቢያዊ አንድነትን የምናጠናክረበት ጊዜ መሆን አለበት በማለት አብራርተዋል።

አሁንም ሆነ ወደፊት ምክርቤቱ በሚያደርጋቸው ውይይቶች ውስጥ የተከሰተውን ሁኔታ ምክንያት በማድረግ በሰብአዊነትና በእርዳታ አቅርቦት ስም በኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ግዛታዊ አንድነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አንፈልግም ያሉት አምባሳደሩ አሁን የሚያስፈልገው ጥንቃቄ በተሞላበት ዲፕሎማሲ የሚደረግ ፈጣንና ህዝብን ያስቀደመ የቀጠናውን ሰላም ያከበረና የተዛቡና በተሳሳቱ መረጃዎችን ያስወገደ የሰብአዊ እርዳታዎች ተደራሽነት መሆኑን ተናግረዋል።  አምባሳደሩ አያይዘውም “ኢትዮጲያዊያን ለሀገር ግንባታቸው እና ለብልጽግናቸው ወሳኝ የሆነውን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ወሳኝ ጊዜ ላይ በሆኑበት በአሁን ጊዜ እኛ አፍሪካዊያን ከኢትዮጲያ መንግስት እና ህዝብ ጎን አብረን እንቆማለን።” በማለት አስረድተዋል።

በተመድ የቻይና ተወካይ አምባሳደር ዳኢ ቢንግ “የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ባለቤትነት ሙሉ በሙሉ ማክበር እንዳለበት ቻይና በድጋሚ ትገልፃለች” በማለት በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። ሩሲያም ተመሳሳይ አቋምን አንጸባርቃለች።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጰያ ቋሚ መልእክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ መንግስት ያወጀው የተናጥል ተኩስ አቁም በክልሉ የሚደረገው የሰብአዊ ድጋፎችን ለማሳደግና ሁሉን አካታች ውይይት ለማድረግ ሰፊ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።  በክልሉ በመንግስት እየተሰሩ ስላሉ ድጋፎች ሊበረታቱና እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል በማለት ያብራሩት አምባሳደር ታዬ በክልሉ የሚደረገው ሰብአዊ ድጋፍ ለማሳደግ በሚል መንግስት የተኩስ አቁም ውሳኔ መወሰኑን አስረድተዋል።

መንግስት ይህን ውሳኔ ቢያሳልፍም የህወሃት ሃይሎች በርካታ ትንኮሳዎችን እየፈጸሙ መሆኑንም አያይዘው ተናግረዋል። መንግስት አሁን ላይ ሰፋ ያለ ሰብአዊ ድጋፍ  እንዲሰራ እድል ከፍቷል ያሉት አምባሳደር ታዬ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እና አምስት የተራድኦ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ያለውን ቀውስ ለመቅረፍ ከሁሉም ወዳጅ ሀገራት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አክለው ገልጸዋል።  

በሀገሪቱ ላይ ያለአግባብ ሊደረጉ የሚገቡ ጫናዎች ሊቆሙ እንደሚገባ አምባሳደሩ ጠይቀዋል። የምክር ቤቱ አባላት ኢትዮጵያ እያለፈችበት ያለው ፈተና ሊገነዘቡ ይገባል ያሉት አምባሳደር ታዬ መንግስት ሰላምን ለማምጣት እየወሰደ ስላለው እርምጃ ተገቢው እውቅና መሰጠት አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም