ቀጥታ፡

ከጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምርቶች 140 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኘ

ደብረ ብርሃን፣ ሰኔ 26 ቀን 2013 (ኢዜአ) ወደ ተለያዩ ሃገራት ከተላኩ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምርቶች 140 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ የ2013 በጀት ዓመት  የ11 ወር ዕቅድ አፈጸጸሙ ላይ በደብረ ብርሃን ከተማ በተወያየበት ወቅት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ስለሺ ለማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፉን ውጤታማነት ለማስፋፋት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተገንብተው ወደ ስራ ገብተዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች  ባለፉት 11 ወራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የፈጠረውን ጫና ተቋቁመው ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ አቅርበው 140 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።

የምርቱ መዳረሻዎች አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ቱርክ፣ ጣልያን እና ጀርመን መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት 90 በመቶ የነበረው የውጭ ገበያ አቅርቦት ወደ 60 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቅሰዋል።

የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉን በማዘመንና ጥራትን በመጠበቅ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ዘንድሮ በመስኩ ምሁራን 22 ጥናትና ምርምሮች ተደርገው 11ዱ ተጠናቀው ለባለድርሻ አካላት እንዲደርሱ መደረጉን ጠቁመዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ በ2013/2014 የምርት ዘመን የዘርፉን የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት ለማቃለል በ150 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 170 ሺህ ቶን ጥሬ ጥጥ ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ ነው።

የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ተመራማሪዎች የበኩላቸውን እገዛ በማድረግ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በኢንስቲትዩቱ የላቦራቶሪ ፍተሻ ባለሙያ ወይዘሪት ሰላም ገበየሁ በበኩላቸው "ኢንስቲትዩቱ በማማከር፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በውጭ ሃገር የገበያ ትስስር መፍጠር ባለሃብቶችን ይደግፋል" ብለዋል።

በቀጣይ ሃገሪቱ በዘርፉ የተሻለ ገቢ እንድታገኝና ባለሃብቶችም ምርታማነታቸው እንዲጨምር ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች በደብረ ብርሃን በሚገኙ ሁለት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ቅጥር ግቢ 2 ሺህ ያህል አገር በቀል ችግኞችን በመትከልም አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ  እንዳሉት፤ ከመሬት መራቆት ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን የአየር ንብረት መዛባት በዘላቂነት ለመከላከል ችግኝ መትከል ወሳኝ ነው።

"በተለይም በሃገሪቱ የኢንዱስትሪ ዘርፉ መስፋፋት ከአየር ንብረት ለውጥ መዛባት ጋር ተያይዞ ችግሩ እንዳይባባስ የችግኝ ተከላው ወሳኝ መፍትሄ ነው" ብለዋል።

እንደ ሃገር የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመከላከል የተያዘውን ግብ ስኬታማ ለማድረግ የችግኝ ተከላ ሥራው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም