ቀጥታ፡

ኤጀንሲው የፓስፖርት አቅርቦት እጥረት መፍታቱን አስታወቀ

አዳማ፤ ሰኔ 26/2013 (ኢዜአ) የዜግነት፣ ኢሚግሬሽንና ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጄንሲ አንድ ሚሊዮን 500ሺህ ፓስፖርት ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የነበረውን የአቅርቦት እጥረት መፍታቱን አስታወቀ ።

ኤጀንሲው በተቋማዊ ሪፎርም ዙሪያ ያከናወናቸውን ስራዎች ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭና ሰላም ጉዳዩ ቋሚ ኮሚቴ ጋር በአዳማ እየገመገመ ይገኛል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማል በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኤጀንሲው ከለውጡ ወዲህ በጀመረው ተቋማዊ ሪፎርም የአገልግሎት አሰጣጡን በማህበራዊ  ትስስር ገፅ አድርጓል።

በተለይ ከፍተኛ የሆነ የፓስፖርት እጥረት ተከስቶ እንደነበር ያሰታወሱት አቶ ሙጂብ፤ በአሁኑ ወቅት ችግሩን ሙሉ በሙሉ በማቃለል  አንድ ሚሊዮን 500ሺህ ፓስፖርት ወደ ሀገር ውስጥ አስገብተናል ብለዋል።

በዚህም የአቅርቦት ችግር ከመፈታቱም ባለፈ የፓስፖርትና የቪዛ አገልግሎት ዜጎች በያሉበት ሆነው እንዲያገኙ የማህበራዊ ትስስር ገፅ ስርዓት ተግባራዊ መደረጉን አመልክተዋል።

አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ጋምቤላና ቤንሻንጉልን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ቅርንጫፎች መከፈቱን ጠቅሰው ፤የመውጫ ና መግቢያ  ድንበሮች ላይ አስፈላጊውን ቴክኖሎጂ በመዘርጋት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የመልካም አስተዳደር ችግር በተለይ ፓስፖርት በህገ ወጥ መንገድ ለማውጣት መሞከር፣ መግባትና መውጣት የማይገባቸውን ሰዎች በማስወጣትና በማስገባት ተግባር የተሳተፉ 50  የኤጀንሲው ሠራተኞች ከድርጊታቸው እንዲታረሙ  መደረጉን  ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

ሀሰተኛ ፓስፖርቶችን ለመለየት በኢትዮጵያ አየር መንገድ የፎሬንሲክ ላቦራቶሪ በመግጠም እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለፓስፖርት መመዝገቢያ የሚያገለግሉ ቴክኖሎጂዎች ከወቅቱ ጋር የማይሄዱ መሆናቸው፣ የሰው ሃይል እጥረት አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች በክፍተት አንስተዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደስላሴ በበኩላቸው፤ ኤጀንሲው አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግና አዳዲስ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ በኩል ያከናወናቸው ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የተገልጋይ እንግልት የሚቀንስ በማህበራዊ ትስስር ገፅ ምዝገባና የአቅርቦት እጥረት ችግር መቃለሉ መልካም እንደሆነ ተናግረዋል።

የሰው ሃይል እጥረት፣ የባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር ክፍተት በተለይ የወሳኝ ኩነቶች የአሰራር ስርዓት መዘመን እንዳለበትም ሰብሳቢው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም