የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሰሞኑን በሶማሌ ክልል የተፈጸመውን ጥቃት አወገዘች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሰሞኑን በሶማሌ ክልል የተፈጸመውን ጥቃት አወገዘች

አዲስ አበባ ሐምሌ 30/2010 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሶማሌ ክልል የተፈጸመውን ጥቃትና ዝርፊያ አወገዘች፡፡ በክልሉ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት፣ ካህናትና ምዕመናን ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ፣ የንብረት ውድመትና ዝርፊያውን መንግሥት በአፋጣኝ ሊያስቆመው እንደሚገባም ቤተክርስቲያኗ ጠይቃለች፡፡ ከሁለት ቀናት በፊት በሶማሌ ክልል በተካሄደ ሃይማኖት ተኮር ጥቃት የሰባት አገልጋዮች ህይወት ማለፉንና የጅግጅጋ ቅድስት ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያንን ጨምሮ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ ለሙሉ በቃጠሎ መውደማቸውን ቤተክርስቲያኗ አስታውቃለች። በተጨማሪም የቤተክርስቲያኗን ጳጳስ መቀመጫ ህንፃ ጨምሮ ሱቆች መውደማቸውንና መኪናና ልዩ ልዩ ንብረቶቹም በአደጋ ፈጣሪዎቹ መዘረፋቸው ተገልጿል። ጉዳዩን በማስመልከት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ በጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ለሀገር ሰላምና አንድነት በምትሰራዋ ቤተክርስቲያን ላይ ይህን መሰሉ ግፍ ሊፈጸምባት እንደማይገባ አስገንዝበዋል፡፡ “በመላው አገራችን ሰላም ፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ መከባበርና መቻቻል እንዲዳብር የአመራር መርህ በስፋትና በጥልቀት እየተሰጠ ባለበት ወቅት የአገርና የወገን ፍቅር ስሜት የተለየው የጭካኔ ስራን መስራት ከኢትዮጵያውያን ዜጎች የሚጠበቅ ተግባር ሆኖ አላገኘነውም “ ብለዋል በጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፡፡ በግጭቱ የእምነቱ ተከታዮች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ የተደረገ ሲሆን ህይወታቸውን ለማትረፍ በጅግጅጋ ቅዱስ ሚካኤልና በጎዴ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያናት ተጠልለው እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል። ለሶስት ቀናት ያለ ምግብ፣ ውሃና ልብስ በቅጥረ ቤተክርስቲያን ተጠልሎ ላለው ህዝብም መንግስት በህይወት የመቆየት ስጋቱን ከማስወገድ ጀምሮ አስፈላጊውን የምግብ የመጠለያና የአልባሳት ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባው አሳስበዋል። አብረው በኖሩ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ግጭት፣ አለመግባባትና መቃቃር ወደ ሌሎችም አካባቢዎች ተስፋፍቶ የበለጠ ጥፋት ከማስከተሉ በፊት የሚለከታቸው አካላት አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎችም ከዚህ የበለጠ ሮሮ ሳይሰማ ህግ የማስከበር ስራ እንዲሰሩና ከህዝብ የተረከቡትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡም ጠይቀዋል። መላ የእምነቱ ተከታዮች ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበው ህብረተሰቡ በዘር፣ በሃይማኖትና በጎሳ ሳይለያይ ይህን እኩይ ድርጊት ሊያከሽፍ እንደሚገባው መክረዋል፡፡ በሶማሌ ክልል የተፈጠረውን ጨምሮ መሰል አደጋዎች እንዲርቁ ነገ በሚጀመረው ፆመ ፍልሰታ ለማርያም ሱባኤ እንዲያዝና ምህላ እንዲደረግ እንዲሁም በአደጋው ህይወታቸውን ላጡትም በመላው ገዳማትና አድባራት ጸሎተ ፍትሃት እዲደረግ ፓትርያርኩ አዘዋል፡፡