"የተከሰስኩበት ወንጀል ሃሰት መሆኑ ቢረጋገጥም ከእስር ልፈታ አልቻልኩም" - ኢዜአ አማርኛ
"የተከሰስኩበት ወንጀል ሃሰት መሆኑ ቢረጋገጥም ከእስር ልፈታ አልቻልኩም"
ባህርዳር፣ ሰኔ 26 ቀን 2013 (ኢዜአ) "በተቀነባበረ ሴራ ጥፋተኛ ከተባልኩበት የሰው መግደል ወንጀል ነጻ መሆኔ በህግ ቢረጋገጥም 5 ዓመት ከ11 ወር ከቆየሁበት ማረሚያ ቤት ልፈታ አልቻልኩም" ሲሉ በሰሜን ሸዋ ማረሚያ ቤት የሚገኙ የህግ ታራሚ ገለጹ።
በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃና ወደራ ወረዳ ሰላ ድንጋይ ከተማ ነዋሪ የነበሩት ወይዘሮ አዛለች ቤተምንዳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ 'የእንጀራ ልጇን ደብደባ ገድላለች' በሚል ክስ ተመስርቶባቸው ለእስር ተዳርገዋል።
የአስር ዓመት የትዳር አጋራቸው የነበሩት ባለቤታቸው ከዚህ አለም በሞት በመለየታቸው እርሳቸው ያልወለዷትን የባለቤታቸውን ልጅ ይዘው ይኖሩ እንደነበር ተናግረዋል።
ልጅቱን በማስተማር የባለቤታቸውን አደራ ለመወጣት እየጣሩ ባለበት ድንገት ልጅቱ ከቤት መሰወሯን አስረድተዋል።
'የአባቷ ቤተሰቦች ልጅቷን እያወቁ ደብቀዋታል' የሚል እምነት እንደነበራቸው ያስታወሱት ወይዘሮ አዛለች፤ "ልጅቷ ሞተች" በሚል የሃሰት ክስ ተመስርቶባቸው ለእስርና እንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
በወቅቱ "ልጅቷን ገለሽ ቀብረሻታል" በሚል ጥርጣሬ ፖሊስ አካባቢውን ከመቆፈር በተጨማሪ ሽንት ቤት በማስመጠጥ እንዳጣራ ጠቅሰው፤ ተጨባጭ ማስረጃ ባለመገኘቱም እውነቱን አውጪ በማለት በጨለማ መደብደባቸውንም አስታውሰዋል።
በተቀነባበረ መንገድ በተመሰረተባቸው የግድያ ክስ ጥፋተኛ ተብለው 20 ዓመት ፅኑ እስራትና የ5 ዓመት የማህበራዊ ዕግድ ተፈርዶባቸው እንደነበር አስታውሰው፤ "ሞተች የተባለችው ግለሰብ ከጥር ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአካል ከተደበቀችበት መጥታ በሰላም እየኖረች ነው" ብለዋል።
"ይህም በህግ የተረጋገጠ ቢሆንም እስካሁን ከእስር አልተፈታሁም፤ በዚህም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ደርሶብኛል'' ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
የደረሰባቸውን በደል በማስረዳት ከእስር እንዲፈቱ ያቀረቡት ተደጋጋሚ ቅሬታ ሰሚ በማጣቱ ተስፋ ቆርጠው የሚሆነውን መጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።
"መንግስትና ህዝብ ካለ በደሌ ተሰምቶ ከእስር ልፈታ ይገባል፤ አጥፊዎቹም ይጠየቁልኝ፤ በእስር እያለሁ ንብረቴ በሃራጅ በመሸጡም ስፈታ የማርፍበት ቦታ የለኝም፤ መንግስት መቋቋሚያ ቢሰጠኝ እፈልጋለሁ" ሲሉም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የይቅርታና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፀሐይነህ አጥናፉ በበኩላቸው፤ ግለሰቧ በተመሰረተባቸው ሃሰተኛ ክስ ያለአግባብ ለእስር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 20 ዓመት ፅኑ እስራት ተወሰኖባቸው 5 ዓመት ከ11 ወር በማረሚያ ቤቱ መቆየታቸውንም አረጋግጠዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ በይቅርታ መመሪያ ቁጥር 30/2010 ዓ.ም መሰረት አንድ የህግ ታራሚ በሃሰተኛ ማስረጃ ወይም ምስክርነት ምክንያት ጥፋተኛ የተባለ መሆኑን ማረጋገጥ ከተቻለ ያለ ቅድመ ሁኔታ በይቅርታ ተጠቃሚ እንዲሆን ይደረጋል።
በዚህ መመሪያ መሰረት ግለሰቧ ጉዳያቸው ተጣርቶ በይቅርታ እንዲፈቱ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለክልሉ መስተዳደር ምክር ቤት በግንቦት ወር ውስጥ መላኩን ተናግረዋል።
ጉዳያቸው የቅድሚያ አጀንዳ እንዲሆን ለመስተዳደር ምክር ቤቱ መቅረቡን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ የሚጠበቀው የምክር ቤቱ ውሳኔ ብቻ መሆኑን አመልክተዋል።
"ግለሰቧን የሚክስ ህግ ባይኖርም ካሳቸው ጥፋተኞችን በህግ እንዲቀጡ ማድረግ ነው" ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በበላይ አመራሩ የሚወሰን ካለ ሊካሱ እንደሚችልም ጠቁመዋል።
ግለሰቧን በሃሰት በመመስከርና ክስ በመመስረት እንዲቀጡ ያደረጉ ግለሰቦች በህግ እንዲጠየቁ ለአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንና በተዋረድ ለዞኑ ዐቃቤ ህግ መምሪያ በደብደቤ እንደተገለጸም አስታውቀዋል።
እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ የሰሜን ሸዋ ዞን ዐቃቤ ህግ መምሪያ የወንጀል ዐቃቤ ህግ ዮሐንስ ወልደገሪማ "የሀሰት መስካሪዎችን ተጠያቂ የሚያደርጋቸው ጉዳይ የለም" ሲሉ በስልክ ገልጸዋል።
በፖሊስ ምርመራ ወቅት በሽንት ቤት ውስጥ አጠራጣሪ ጉዳዮች መገኘታቸው ወደ ውሳኔ አዝማሚያ እንዲደርስ ማድረጉን ጠቁመው፤ ግለሰቧ አሁን ያለምንም መጓተት ሊፈቱ እንደሚገባ ተናግረዋል።
መስካሪዎቹ አንዱ የሰባት ዓመት ህፃን ሲሆን በወቅቱ "ልጇን በዘነዘና መትታ ስትጥላት አይቻለሁ" ብሎ መመስከሩን አስታውሰው፤ "ህጻኑ አይታለልም ተብሎ በህግ ስለሚታመን በሃሰተኛ ምስክር አይጠየቅም" ብለዋል።
ሌሎች ሁለቱ ምስክሮችን በተመለከተም "ሲጣሉና ሲጨቃጨቁ አይተናል ይበሉ እንጂ መትታ ስትገላት አየን ብለው የመሰከሩ ባለመሆናቸው የሚያስጠይቃቸው ጉዳይ የለም፤ ክስ መመስረትም አዋጭ አይደለም" ሲሉ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የህግ ታራሚዎች የፍትህ አስተዳደር ዳይሬክተር ረዳት ከሚሽነር አማረ ወርቁ በበኩላቸው፤ ከወንጀል ንፁህ ሆነው እያለ ያለ ጥፋታቸው በማረሚያ ቤት ያሉት ግለሰብ በፍጥነት እንዲፈቱ መረጃቸው ተጣርቶ መላኩን ገልጸዋል።
ሀሰተኛ የማስረጃ ምንጮችና ምስክሮች መበራከት ብዙዎች ባልተገባ ክስ ጥፋተኛ ተብለው በማረሚያ ቤቶች እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ለዚህም ፖሊስ፣ ፍርድ ቤትና ዐቃቤ ህግ ተቀናጅተው አለመስራት፣ ጥልቀት ያለው ምርመራና ማጣራት አለማድረጋቸው አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ተቀናጅቶ መስራትና የሃይማኖት አባቶችም ምዕምናኑን በማስተማር ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ግለሰቧ በደረሰባቸው በደልና ግፍ ሊካሱ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ "እንደ ተቋም የሚደረግ ድጋፍ ካለ ይታሰብበታል" ብለዋል።