ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ እንዲወጡ በሚደረገው ጫና ላይ የሌላ አገር ተጽእኖ ሊኖር ይችላል ... ዶ/ር ብርሃኑ ሌንጂሶ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ እንዲወጡ በሚደረገው ጫና ላይ የሌላ አገር ተጽእኖ ሊኖር ይችላል ... ዶ/ር ብርሃኑ ሌንጂሶ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ እንዲወጡ በሚደረገው ጫና ላይ የሌላ አገር ተጽእኖ ሊኖር ይችላል ሲሉ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ ገለጹ።
ሳዑዲ ዓረቢያ ፈቃድ ያላቸውን ጨምሮ 40 ሺህ ኢትዮጵያውያን ከአገሯ እንዲወጡ መወሰኗን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን ለመመለስ እየሰራ ይገኛል።
እስካሁን ባለው ሂደትም በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በሳዑዲ ዓረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጠረው ችግር ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ነው ያመለከቱት።
ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጀመረችና ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር አቋም በመያዟ በተለያዩ አካባቢዎች ጫና እየተደረገባት እንደሚገኝም አመልክተዋል።
በተለይ የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ግብጽ ተለዋዋጭ ባህሪ በማሳየት ስምምነት እንዳይኖር በማድረግ የተለያዩ ጫናዎች እንዲፈጠሩ እየሰራች መሆኑን በአብነት ጠቅሰዋል።
በተለይ ግብጽ በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ የያዘችውን ኢ - ፍትሃዊ አቋም በተመለከተ የዓረቡን ዓለም ከጎኗ በማሰለፍ ተቀባይነት እንዲያገኝ ጥረት እያደረገች መሆኑን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ግብጽ በተለያዩ ዘዴዎች ኢትዮጵያ ላይ ጫና በመፍጠር የሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌትን ለማደናቀፍ ቆርጣ መነሳቷንም ተናግረዋል።
ሳዑዲ ዓረቢያ ከወትሮው በተለየ መልኩ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸውን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከአገሯ እንዲወጡ ማድረጓ "ግብጽ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ያላትን ግንኙነት ተጠቅማ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ያደረገችው ሊሆን ይችላል" የሚል እምነት እንዳላቸው ነው ያመለከቱት።
ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ እንዲወጡ መደረጉ ግብጽ በዓረብ ሊግ ውስጥ ያላትን ተጽእኖ ፈጣሪነት ተጠቅማ "ጫና ለመፍጠር የሸረበችው ሴራ ነው" የሚል ድምዳሜ መኖሩንም አብራርተዋል።
ግብጽ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችንና ተጽእኖ ፈጣሪ አገሮችን በመማጸን በዓባይ ወንዝ ላይ የያዘችው ኢ- ፍትሃዊ አቋም ተቀባይነት እንዲያገኝ እየሰራች መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ከዚህ አኳያ ሲታይ ኢትዮጵያ ያላትን ፍትሃዊ አቋም በማሳወቅ ረገድ በሚፈለገው ደረጃ እየሰራች አለመሆኑንም ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከ80 በመቶ በላይ ለዓባይ ውሃ አስተዋጽኦ የምታደርግና 60 በመቶ ህዝቧ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የማያገኝ መሆኑን በማሳወቅ ረገድ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ እንደሚያስፈልግም መክረዋል።
ኢትዮጵውያን የትኛውንም ዓይነት ጫና ተቋቁመው የተጀመሩ አገራዊ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ የሚችሉት አንድነታቸውን ሲጠብቁ መሆኑንም ዶክተር ብርሃኑ አውስተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎችን ወደ አገር ለማምጣት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ፈቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን እንዲወጡ መደረጉ ከጀርባው የሌሎች አገራት እጅ ሊኖር እንደሚችል ገልጸው፤ ችግሩን ለመፍታት በዲፕሎማሲው መስክ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅትም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉ ዜጎች ቅድሚያ ተሰጥቶ ወደ አገር ቤት የመመለሱ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።
ዜጎች በአገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ ህገ-ወጥ ስደትን ከምንጩ ማድረቅ፣ የማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብትና የጸጥታ ችግሮችን ማቃለል ይጠበቃልም ብለዋል።