የትግራይ ሕዝብ የአሸባሪውን የህወሓት ቡድን አደገኛ አካሄድ ባገኘው የጥሞና ጊዜ በአግባቡ ሊረዳው ይገባል…በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ሕዝብ የአሸባሪውን የህወሓት ቡድን አደገኛ አካሄድ ባገኘው የጥሞና ጊዜ በአግባቡ ሊረዳው ይገባል…በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን
ሰኔ 26/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን በዘራው የዘረኝነት መርዝ የህዝቦች አንድነት እንድላላ እና እርስ በርስ እንድፋጁ ያደረገ አጥፊ ኃይል በመሆኑ የትግራይ ሕዝብ የዚህን አደገኛ ቡድን አካሄድ ባገኘው የጥሞና ጊዜ በአግባቡ ሊረዳው ይገባል ሲሉ በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገለጹ።
መንግስት በቅርቡ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱንና የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉን ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የመከላከያ ሠራዊቱ ከትግራይ ክልል መውጣትና የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔን በተመለከተ በሱዳን ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱ በሱዳን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ባደረጉት ገለጻ፣ አሸባሪው የህመሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ሠራዊቱ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ላይ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በሕግ ማስከበር ዘመቻው የአሸባሪውን ቡድን ሙሉ በሙሉ በማዳከም የተወሰኑ መሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸው፤ ከፊሉን በመደምሰስ ቀሪዎቹ ደግሞ በየሸለቆው ተደብቀው ወጣቱን ላልተገባ እልቂት እየዳረጉ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በዚህም ሂደት የእርሻ ስራም ሆነ የእርዳታ አቅርቦት እየተስተጓጎለ በመምጣቱ ሕዝቡን ከከፋ እልቂት ለመታደግ የመንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ እና ሠራዊቱን ከትግራይ ለማስወጣት እንደወሰነ አምባሳደሩ አክለው አስረድተዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊ ኢትዮጵያውን በበኩላቸው ለተደረገላቸው ወቅቱን የጠበቀ ገለጻ አመስግነው፣ መንግስት የዜጎችን ሕይወት ለመታደግና የትግራይ ሕዝብም የጥሞና ጊዜ እንዲያገኝ የተናጠል ተኩስ አቁም ማድረጉን አድንቀዋል፡፡
ሠራዊቱን ከትግራይ ማስወጣቱ ትክክለኛ እና ወቅታዊ ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በዘራው የዘረኝነት መርዝ የህዝቦች አንድነት እንደላላ እና እርሰ በርስ እንድፋጁ ያደረገ አጥፊ ኃይል በመሆኑ የትግራይ ሕዝብ የዚህን አደገኛ ቡድን አካሄድ ባገኘው የጥሞና ጊዜ በአግባቡ ሊረዳው ይገባልም ነው ያሉት።
ለአሸባሪ ቡድኑ የጦር መሣሪያም ሆነ ሌላ ለጥፋት የሚውል ድጋፍ ከውጭ እንዳይገባ መንግስት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡
ማናቸውንም የአሸባሪው ቡድን ትንኮሳ ለመግታት በትኩረት እንዲሰራ በመጠየቅ፣ ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ ማረጋገጣቸውን ከሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።