የባለ ልዩ ጣዕም የቡና ቅምሻ ውድድር ቀጣይ ሳምንት ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የባለ ልዩ ጣዕም የቡና ቅምሻ ውድድር ቀጣይ ሳምንት ይካሄዳል
አዲስ አበባ ሰኔ 26/2013(ኢዜአ) የባለ ልዩ ጣዕም የቡና ቅምሻ ውድድር በቀጣዩ ሳምንት እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ እንደገለጹት በውድድሩ ቡና የሚያቀርቡ አርሶ አደሮችና ቡና አቅራቢ ነጋዴዎች የቡና ምርታቸው የተሻለ ዋጋ እንዲኖረው ለማስቻል ነው።
የኢትዮጵያ ቡና አምራች አርሶ አደሮች የልፋታቸውን ያክል ገቢ ሳያገኙ መቆየታቸውንና አገሪቱም ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም ሳታገኝ መቆየቷን ጠቅሰዋል።
ሆኖም ችግሩን ለመፍታት በመሰራቱ ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያው የካፕ ኦፍ ኤክሰለንሲ የቡና ጣዕም ውድድር በጥሩ ዋጋ መሸጡን ተናግረዋል።
በውድድሩ አንድ ኪሎ ግራም ቡና ከ400 ዶላር በላይ እንዲሸጥ መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡
በሁለተኛው ዙር የባለ ልዩ ጣዕም /የካፕ ኦፍ ኤክሰለንሲ/ ውድድር ደግሞ ካለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት ለማግኘት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ በውድድሩ ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ከዩ ኤስ ኤይድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ስልጠና እና እገዛ መደረጉንም ተናግረዋል።
በቀጣይ ሳምንት ረቡዕ በኦላይን ለጨረታ የሚቀርቡት የቡና ምርቶች አገሪቷ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም አንስተዋል።
በጨረታው ላይ ከ33 ሀገራት ተውጣጡ ከ180 በላይ ቡና ገዢዎች ተሳታፊ ለመሆን መመዝገባቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፅዮን ተክሉ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከቡና ምርት የተሻለ ገቢ እንድታገኝ ባለስልጣኑ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የቡና አምራች አርሶ አደሮችን ለማበረታታት ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በዘንድሮው ውድድር 1 ሺህ 400 ኪሎ ግራም ቡና በማቅረብ አራተኛ የወጡት በሲዳማ ክልል ቦና ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ናሬ ዋሬ የውድድሩ ጠቀሜታ ላቅ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት 1 ሺህ 200 ኪሎ ግራም ቡና አቅርበው ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘታቸውንም አስታውሰዋል።