በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ፖለቲካዊ ጫናዎች የዓለም ዓቀፍ ህግ መርሆዎችን የጣሱ ናቸው - አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ፖለቲካዊ ጫናዎች የዓለም ዓቀፍ ህግ መርሆዎችን የጣሱ ናቸው - አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ
ሰኔ 26 ቀን 2013 (ኢዜአ) “በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ፖለቲካዊ ጫናዎች የዓለም ዓቀፍ ህግ መርሆዎችን የጣሱ ናቸው” ሲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ።
ጫናዎቹ ኢትዮጵያ ያሉባትን ችግሮች ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት እንደሚያደናቅፉም አመላክተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ ትናንት በጠራው ስብሰባ መክሯል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ “ኢትዮጵያ ሁሉን አካታች የሆነ ውይይት ለማድረግ ፍኖተ ካርታ እያዘጋጀች ነው” ብለዋል።
አገሪቱ በቅርቡ ካካሄደችው ሰላማዊ ምርጫ ማግስት ጀምሮ ጠንካራ፣ አንድነቷ የተጠበቀና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በዚህም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንደሚፈጠር ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በመግታት አርሶ አደሩ እንዲያርስና ለሌሎች አገራዊ አጀንዳዎች ቅድሚያ በመስጠት መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ርምጃ ስለመውሰዱ አስረድተዋል።
በክልሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸው፤ “ከሁሉም አጋሮች ጋር መስራታችን ይቀጥላል” ብለዋል።
በትግራይ ክልል ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ አውስተው፤ የጸጥታው ምክር ቤት የመንግስትን ጥረት በማገዝ ረገድና የተኩስ አቁም ርምጃ ተፈጻሚነት ላይ ገንቢ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ፖለቲካዊ ጫናዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው የገለጹት አምባሳደር ታዬ፤ ጫናዎቹ የዓለም ዓቀፍ ህግ መርሆዎችን የጣሱ እንደሆኑም አስረድተዋል።
የበዛና ተገቢ ያልሆነ ጫና ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ከገባችበት ችግር የማያወጣት መሆኑንም አመልክተዋል።
የኬንያው ልዩ መልዕክተኛ ማርቲን ኪማኒ በበኩላቸው በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ መንግስት ያደረገውን የሰብዓዊ ድጋፍ አድንቀዋል።
የመንግስት ጥረት ይበልጥ ፍሬ እንዲያፈራም የሰብዓዊ ድጋፍ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ጥረታቸውን በእጥፍ ማሳደግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በቅርቡ የተካሄደው ምርጫ አዎንታዊ ውጤት እንደታየበት ገልጸው፤ የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን ከአንዳንድ ጥቃቅን ችግሮች በስተቀር አጠቃላይ የቅድመ ምርጫና የምርጫ ወቅት ሂደት ሰላማዊና ተቀባይነት ያለው እንደሆነ መግለጹን ጠቅሰዋል።
የምርጫው ሰላማዊነትን ጨምሮ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ በመግለጽ ፤ የጸጥታው ምክር ቤት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በትግራይ ክልል የሚደረገውን ሰብዓዊ ድጋፍ በማበረታታት ጥንቃቄ የተሞላበት ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ርምጃ አድንቀው፤ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ርምጃውን በማድነቅ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።