ቀጥታ፡

"ኢትዮጵያውያን በምርጫው ሀገር እንድታሸንፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይተዋል"... ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን በምርጫው ሀገር እንድታሸንፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይተዋል፤ ለዚህም የላቀ ክብር ይገባቸዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ምክር ቤት በዘንድሮው ምርጫ ለተፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባዘጋጀው የምስጋና መርሃግብር ላይ ነው።

በመርሃግብሩ የሃይማኖት አባቶች፣ ፖለቲከኞች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር መንግስት የዘንድሮውን ምርጫ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከተከናወኑ ምርጫዎች በተለየ መልኩ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነጻ ምርጫ ለማከናወን አበክሮ ሰርቷል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ተጋፍጠው ድምጽ በመስጠት "ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ" ንቁ ተሳትፎ አድርገዋል ብለዋል።  

የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የጸጥታ ተቋማት እንዲሁም ፍርድ ቤቶች ለምርጫው መሳካት አይተኬ ሚና እንደነበራቸውም አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ምርጫ ማካሄድ የቻለችው ሁላችንም ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ  በመስራታችን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ምርጫ ቦርድ አደረጃጀቱን በአጭር ጊዜ አስተካክሎ ለምርጫ ስኬት ያከናወነውን ተገባርንም አድንቀዋል።

ኢትዮጵያውያን በምርጫው "ማሸነፍ፤ መሸነፍ" ከሚለው የፖለቲካ ሃሳብ ይልቅ ሀገር እንደምትቀድም በተግባር ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን በምርጫው ያደረጉት ተሳትፎ በኢትዮጵያ ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትምህርት የሰጠ መሆኑን ጠቁመው፤ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢትዮጵያን አምነው በምርጫው በመሳተፋቸው አመስግነው ፓርቲያቸው አገር በጋራ እንደሚገነባ በፅኑ ያምናል ብለዋል።

በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተባብረውና ተጋግዘው አገራቸውን በማቅናት ማሻገር ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በምርጫ ፉክክሩ የብልጽግና ፓርቲ አሸናፊ የሚሆን ከሆነ በምርጫው የተፎካከሩ የፓርቲዎችን እንደተሳትፏቸው መጠን ከታች ጀምሮ በመንግስት መዋቅር ውስጥ እንደሚያሳትፍም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክርቤት ፕሬዝዳንት ዶክተር ንጉሱ ለገሰ በበኩላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጀመሩት በሃሳብ የመፎካከርና በመርህ ላይ የተመሰረተ ትብብር የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል።

ነገር ግን ይህ ገና ጅምር በመሆኑ "ቀሪ የቤት ስራዎች ከፊት ለፊታችን ይጠብቁናል" ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የዘንድሮውን ሀገራዊ ምርጫ ፈተና በሆኑ የውስጥና የውጭ ችግሮች ውስጥ ሆና ማከናወኗን ያስታወሱት ደግሞ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሔል ባፌ ናቸው።

ሆኖም "ኢትዮጵያውያን ከችግሮች ሁሉ በላይ መሆናቸውን በምርጫው አሳይተዋል" ነው ያሉት።

ኢትዮጵያዊያን እንደ ሀገር ትልቅ ተስፋ ሰንቀናል፤ ለዚህ ደግሞ ከታሪካችን ተምረን ወደ ፊት መሄድ አለብን ብለዋል።

በኢትዮጵያዊ አንድነት ተመስርተን የምንፈጥረው ፈውስ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ያወጣታልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም