ቀጥታ፡

አሁን ወጣቱ የሚጠየቀው ጊዜውን፣ እውቀቱንና ጉልበቱን ለልማት እንዲያውል ነው ...የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ አሁን ባለው ነበራዊ ሁኔታ ወጣቱ የሚጠየቀው ጊዜውን እውቀቱንና ጉልበቱን ለልማት እንዲያውል እንጂ ሌላ አይነት መስዋዕትነት አይጠበቅበትም ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።

የሰላም ሚኒስቴር ለመጀመሪያው ዙር የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ሰልጣኞች ስልጠናና ስምሪት ስኬታማነት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት የምስጋና እና እውቅና መርሃ ግብር አካሂዷል።

ከተቋማቱ መካከል ከመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ከስምንት በላይ ዘጋቢ ፊልሞችን በመስራትና በማስተባበር የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቶታል።

የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል እንደገሉጹት በመጀመሪያው ዙር ከ11 ሺህ በላይ ወጣቶች የ45 ቀናት ስልጠናቸውን አጠናቀው ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለስራ ተሰማርተዋል።

የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ስልጠናውን አጠናቀው ወደ ስራ እስከሚሰማሩ በአጀንዳ ቀረፃ፣ በስልጠናና ማኑዋል ዝግጅት ለተሳተፉ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ክልሎች እና ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምስጋና አቅርበዋል።

የምስጋናና እውቅና መርሃ ግብሩ በዘርፉ የሚሳተፉ አካላት በቀጣይ ተጨማሪ የቤት ስራ የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ የነገ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ሃላፊነት ጭምር እንዳለባቸው ለማሳየት ነው ብለዋል።

ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት የመጀመሪያ ሰልጣኞች በሰላም፣ በግብርና፣ በትምህርት በከተማ ልማትና አካባቢ ውበት እንዲሁም በሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች ተሰማርተው ማህበረሰብ በማገልገል ላይ ናቸው ብለዋል።

የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች ከትውልድ ቀያቸው ርቀው ሂደው የሚሰሩ በመሆኑ ከአካባቢያቸው አልፈው የሀገራቸውን ወግና ባህል መረዳት ያስችላቸዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ባለው ነበራዊ ሁኔታ ወጣቱ የሚጠየቀው ጊዜውን እውቀቱንና ጉልበቱን ለልማት እንዲያውል እንጂ ሌላ አይነት መስዋዕትነት አይደለም ብለዋል ሚኒስትሯ። 

በመሆኑም በመጀመሪያ "ለተለየ ተልዕኮ ነው የምንፈለግ" በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ የዳር ተመልካች የነበሩ ወጣቶችም ሆነ ሰልጣኞች እውነታውን ከተረዱ በኋላ በበጎ ፈቃድ ለመሳተፍ ፍላጎታቸው ጨምሯል ብለዋል።

ወጣቶች በቀጣይም ያላቸውን እምቅ አቅም በማውጣት ለሀገር ግንባታና ለብሄራዊ መግባባት ማዋል እንዳለባቸው አሳስበዋል

ለብሄራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት የተመዘገቡ ወጣቶች ቁጥር እስካሁን ከ100 ሺህ ማለፉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም