ቀጥታ፡

በህዝብ ላይ ክፋት መፈጸምና መሰረተ ልማቶችን ማውደም ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው የሚወገዝ ተግባር... የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2013(ኢዜአ) በህዝብ ላይ ክፋት መፈጸምና መሰረተ ልማቶችን ማውደም ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው የሚወገዝ ተግባር መሆኑን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ ጉባኤው በትግራይ ክልል እርቅ፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ተደጋጋሚ ጥረት ማድረጉን ገልጸዋል።

ጉባኤው ከህግ ማስከበሩ ዘመቻ በፊት ለእርቅና ሰላም ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም በወቅቱ ክልሉን ሲያስተዳድር በነበረው መንግስት ተቀባይነት ማጣቱን ተናግረዋል።

ለሰላም በር በመዝጋት በህዝብ ላይ ክፋት በመፈጸምና መሰረተ ልማቶችን ማውደም ፍፁም ተቀባይነት የሌለው የሚወገዝ የጥፋት ተግባር መሆኑንም ነው ጠቅላይ ፀሐፊው የገለጹት።

ከጥፋት የሚገኝ አሸናፊነት ፈፅሞ ሊኖር አይችልም ሲሉም ተናግረው፤ የትግራይ ህዝብ መንግስት ላቀረበለት የሰላም ጥሪ በጎ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።

"ለትግራይ ህዝብ ጥይት ሳይሆን ዳቦ ነው የሚያስፈልገው" ያሉት ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ለዚህ ደግሞ አርሶ አደሩ በግብርናው ስራ እንዲሰማራ የታጠቁ ሃይሎች የሰላም ጥሪውን እንዲቀበሉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በ2003 ዓ.ም. የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሰባት የሃይማኖት ተቋማትን በአባልነት አቅፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም