በመተከል ዞን የወንበራ ወረዳ ነዋሪዎች ተፈናቃዮችን መልሶ በማቋቋም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በመተከል ዞን የወንበራ ወረዳ ነዋሪዎች ተፈናቃዮችን መልሶ በማቋቋም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገለጹ
አዲስ አበባ ሰኔ 25/2013 (ኢዜአ) በመተከል ዞን ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋምና ወደ ልማት ስራ እንዲገቡ በማድረግ ሂደት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የወንበራ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።
የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት በወቅታዊ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በዞኑ ከሚገኘው የወንበራ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርጓል።
የዞንና የወረዳ የስራ ኃላፊዎች ጨምሮ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከኃይማኖት አባቶች፣ ሴቶችና ወጣቶች ተወካዮች በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በመተከል ዞን በነበረው የጸጥታ ችግር ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ ልማት የሚገቡበት ሁኔታ እንዲፈጠር ጠይቀዋል።
ነዋሪዎቹ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋምና ወደ ልማት ስራ እንዲገቡ በማድረግ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የጸጥታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የተጠናከረ የሰላም ማስከበር ስራ ማከናወንና የቀደመ ትብብርና አብሮነትን መመለስ ይገባል ብለዋል።
የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ሕብረተሰቡ ወደ ልማት ስራዎች እንዲገባ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሕብረተሰቡ ለጋራ ሰላምና ደህንነት ከጸጥታ አካላት ጋር በትብብር እንዲሰራም ጠይቀዋል።
የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ የጸጥታ ኃይሉ የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያከናውነውን ተግባር ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ሊደግፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተቋቋመው የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት በዞኑ ያለውን የጸጥታ ማስከበር ስራ ከታህሳስ ወር 2013 ዓ.ም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ የጸጥታ አካላት መረከቡ የሚታወስ ነው።
ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች ያካተተው ኮማንድ ፖስቱ በዋናነት በመተከል ዞን ሕግን የማስከበር ተልዕኮ ተሰጥቶታል።
ኮማንድ ፖስቱ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጋር በመሆን የተፈናቀሉ ዜጎችን የማቋቋም ስራ እያከናወነም ይገኛል።