ቀጥታ፡

መንግስት የሕግ ማስከበር ግዳጁን በብቃት በመወጣት አጀንዳውን ወደ ሌላ ቀዳሚ ተልዕኮ ማድረጉ የተሻለ ወታዳራዊ ስልት ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 25/2013 (ኢዜአ) የፌዴራል መንግስት የሕግ ማስከበር ግዳጁን በብቃት በመወጣት አጀንዳውን በአገራዊ ቀዳሚ ተልዕኮ ላይ ማድረጉ የተሻለ ወታዳራዊ ስልት መሆኑን ለረጅም ዓመታት በውትድርና ሙያ ኢትዮጵያን ያገለገሉ ከፍተኛ የጦር መኮንንች ገለጹ።

በቀደሙት ዘመናት በአየር ወለድ አባልነት በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ተሰልፈው ኢትዮጵያን በውትድርና ያገለገሉ ሁለት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ከነዚህ መካከል አንዱ የሆኑት ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ኃብተማሪያም ''ወትሮውኑ መንግስት ወደ ትግራይ የገባው ክልሉን በሞግዚትነት ለማስተዳደር አይደለም'' ይላሉ።

የመንግስት ሰራዊት ወደ ትግራይ ሲገባ በአገር ሉአላዊነት ላይ የተደቀነውን ግልጽና የቅርብ አደጋን ለመቀልበስ መሆኑ መረሳት እንደሌለበት ነው አጽንኦት የሰጡት።

እስካሁንም መንግስት ባለፉት ስምንት ወራት ሲያካሂድ የቆየው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ግቡን የመታ መሆኑም መታዘብ እንደሚቻል አብራርተዋል።

በዚህ ወቅትም መንግስት የስልት ለውጥ ማድረጉ ትክክለኛና ተገቢ ውሳኔ መሆኑን ነው ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ያረጋገጡት።

"ወታደራዊ ስልት በባህሪው ግትር አይደለም፤ ስልት ከሁኔታዎች ጋር ተለዋዋጭነት ባህሪ ያለው ነው" ብለዋል።  

'መንግስት ቀዳሚ አጀንዳዬ ነው' ብሎ የጠቀሰውን ሁለተኛው ዙር የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ማካሄድና መደበኛ የክረምት ግብርና ስራ ላይ ማተኮሩ ተገቢ እንደሆነ አመልክተዋል።

ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ሠራዊቱ የቦታ ለውጥ ማሻሻያ በማድረጉ አሸባሪው ሕወሓት ከቁጥጥሩ ውጪ እንደሆነ ማስመሰል ተገቢ አይደለም።

ይልቁንስ በቀጣይ ሊቃጡ የሚችሉ ስጋቶችን ለመከላከል የሚያስችል ቁመና እንዲገነባ ያስችለዋልም ነው ያሉት።

ሌላው የቀድሞ አየር ወለድ አባል የነበሩት ኮሎኔል ታምሩ ኃይሉ እንደሚሉት የአሸባሪዎች ዓላማ የመንግስትን አጀንዳ ማስጣልና ራሱ በቀየሰለት መንገድ እንዲጓዝ ማድረግ ነው። መንግስት ይህን ዓላማ ዋጋ በማሳጣት በራሱ አጀንዳ ለመሄድ መወሰኑ ትክክለኛ አቅጣጫ ነው።

አሸባሪው ሕወሓት ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ስራ በመስራት ሕዝቡን ሲያደናግር መቆየቱንም ጨምረው ይገልጻሉ።

በዚህም ''ሳይገድሉ ገደልን በማለት በህዝቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና ማድረግና በጉልበት ለውጊያ ማሰለፍን ይጠቀማል'' ብለዋል።

ይህ ሁኔታ ሲከሰት መንግስት ለቆ መውጣትና በመደኛ አጀንዳው ላይ ማተኮር ተገቢ እርምጃ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የሽብር ሌላው አስከፊ ገጽታ ሸማቂዎች ከንጹሃን ዜጎች ጋር ተመሳስሎ የተደራጃ ሰራዊትን መተንኮስና ማጥቃቱ መሆኑንም አብራርተዋል ኮሎኔል ታምሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም