ሰሜን ኮርያ ከደቡብ ኮርያ ጋር ልታደርግ የነበረውን ውይይት ሰረዘች

89
ግንቦት 8/2010 ሰሜን ኮርያ ከደቡብ ኮርያ ጋር ዛሬ ልታደርግ የነበረውን ውይይት መሰረዟን አስታወቀች፡፡ የአሜሪካ እና ደቡብ ኮርያ ወታደራዊ ልምምድ በአካባቢው የተሻለ ግንኙነት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ላይ ስጋት ደቅኖበታል በሚል ነው ውይይቱ መቅረቱን ያስታወቀችው። የሀገሪቱ የዜና አውታር ይዞት በወጣው መረጃ በመጪው ሰኔ ወር የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሲንጋፖር ቀጠሮ የያዙለት ውይይት ሊቀር እንደሚችል ጥርጣሬ መኖሩን ጠቁሟል። ፒዮንግያንግ ትናንት ማምሻውን ባወጣችው መግለጫ የአሜሪካና የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ልምምድ ሰሜን ኮሪያ ላይ ያነጣጠረ ነው ብላለች። የሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ልምምድ ሁለቱ ኮርያዎች በተፈራረሙት የፓንሙንጆም የሰላም ስምምነት እና በልሳነ ምድሩ መረጋጋት ላይ ስጋት መፍጠሩን ገልፃለች። የአሜሪካ ብረት ለበስ ቢ-52 ተዋጊ ጀቶች የተሳተፉበት የአሜሪካና የደቡብ ኮርያ የአየር ሃይል ወታደራዊ ልምምድ በእኔ ላይ የተቃጣ ትንኮሳ ነው ብላለች። በመሆኑም ፒዮንግያንግ በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ ሊካሄድ የነበረውን የዛሬውን ጉባኤ ከመሰረዝ ውጭ ሌላ አማራጭ የላትም ብላለች። አሜሪካም ትራምፕና ኪም ጆንግ ኡን ቀጠሮ የያዙለት ውይይት እጣ ፈንታ እንዲለይለት ረጋ ብላ ልታስብ እንደሚገባ ነው ሰሜን ኮሪያ ያሳሰበችው። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ስብሰባ በተያዘለት ቀን መሰረት በፈረንጆቹ የፊታችን ሰኔ 12 በሲንጋፖር እንደሚካሄድ ገልጿል። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ሄዘር ናውሬት “ኪም ጆንግ ኡን አሜሪካና ደቡብ ኮርያ የሚያደርጉትን ወታደራዊ ልምምድና ዓላማውን እንደሚገነዘቡት ከዚህ በፊት ተናግረዋል” ነው ያሉት። በመሆኑም የፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ስብሰባ በታቀደው መሰረት እንዲካሄድ ማድረግ አለብን ነው ያሉት። ዋሽንግተን ከፒዮንግያንግ በኩል የአቋም ለውጥ ስለመኖሩ የደረሳት መልዕክት እንደሌለም ቃል አቀባይዋ ተናግረዋል። ዛሬ በሁለቱ ኮርያዎች መካከል ሊካሄድ ታቅዶ የተሰረዘው ስብስባ በፈረንጆቹ ባለፈው ሚያዚያ 27 የተፈረመው የሰላም ስምምነት ተፈፃሚ በሚሆንባቸው ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ያለመ ነበር። በሰላም ስምምነቱ ሰሜን ኮርያ የኒዩክሌር መርሃግብሯን የምታቋርጥበትን እና የኮርያ ጦርነት በይፋ የሚያበቃበትን ሁኔታ ያካተተ እንደነበር የደቡብ ኮርያ የውህደት ሚኒስቴር አስታውሷል። ማክስ ተንደር የሚል መጠሪያ ያለው የአሜሪካና የደቡብ ኮርያ የአየር ሃይል ልምምድ ከፈረንጆቹ ግንቦት 14 እስከ 15 እየተካሄደ መሆኑን ፔንታጎን ያወጣው መረጃ ያሳያል። ምንጭ፦አልጀዚራ እና  እና ሮይተርስ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም